ዋናተኛው ከተፎካካሪው ጎን ቆሞ ሜዳሊያ አልቀበልም አለ

የሜዳሊያ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ አውስትራሊያዊው ሜዳሊያውን ለመቀበል ከተፎካከሪው ሱን ያን ጎን ለመቆም አልፈቀደም። Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሜዳሊያ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ አውስትራሊያዊው ሜዳሊያውን ለመቀበል ከተፎካከሪው ሱን ያን ጎን ለመቆም አልፈቀደም።

አውስትራሊያዊው ዋናተኛ ማክ ሆርተን የምንግዜም ተቀናቃኙ ከሆነው ቻይናዊ ዋናተኛ ጋር በሽልማት መድረክ ላይ በጋራ አልቆምም በማለት ቁጣውን በአደባባይ ገለጸ።

ማርክ ሆርተን ለዚህ ድርጊቱ እንደ ምክንያት ያቀረበው ቻይናዊውን ዋናተኛ ለዓመታት "የአበረታች እጽ ተጠቃሚ እና አጭበርባሪ ነው" እንደሆነ በመግለጽ ይከሰዋል።

ሁለቱ ተፎካካሪ ዋናተኞች ከዚህ ቀደም በበርካታ የውድድር መድረኮች ላይ ተገናኝተዋል። ትናንት በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የዓለም የውሃ ዋና ቻምፒዮና ውድድር ላይ ቻይናዊው ሳን ያን በ400 ሜትር የነጻ ቀዘፋ ውድድር ማርክ ሆርተንን በመቅደም የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

ከውድድሩ በኋላ በተካሄደው የሜዳሊያ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ግን አውስትራሊያዊው ሜዳሊያውን ለመቀበል መድረክ ላይ ከተፎካከሪው ሱን ያን ጎን ለመቆም አልፈቀደም።

ሞ ፋራህ እና ኃይሌ ገብረሥላሴ ተጣሉ

ኦሌ፡ አራተኛ ሆኖ መጨረስ በቂ አይደለም

ከክስተቱ በኋላ ሱን ያን ለሪፖርተሮች ሲናገር "እኔን አለማክበሩ ችግር የለውም፤ ቻይናን አለማክበሩ ግን ያሳዝናል፤ አዝናለሁ" ብሏል።

የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት የሆነው ሆርተን፤ የተፎካካሪውን እጅ ለመጨበጥም ይሁን አብሮ ፎቶ ለመነሳት አልፈቀደም። ነገር ግን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ጣሊያናዊ ጋር ግን ፈገግታ በተሞላበት መልኩ ፎቶግራፍ አብሮ ሲነሳ ታይቷል።

እአአ በ2014 ላይ ሱን አበረታች መድሃኒት ተጠቅመሃል ተብሎ ለሦስት ወራት ታግዶ ነበር። ዋናተኛው ግን መድሃኒቱን ለልብ ህመም ሲል የምወስደው ነው ሲል ተከራክሯል።

በሁለቱ ዋናተኞች መካከል ያለው እስጣገባ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ላይም መነጋገሪያ ነበር። ሆርተን በልምምድ ላይ ሳለሁ ሆነ ብሎ ውሃ ይረጨኝ ነበር ሲል ቻይናዊውን ይከሳል። "እኔ ግን ንቄ ችላ አልኩት። የአበረታች መድሃኒት ተጠቅሞ ለሚያጭበረብር አትሌት ጊዜ የለኝም" ሲል ተናግሮ ነበር።

በሌላ ወቅት "አበረታች ዕጽ መጠቀማቸው የተረጋገጠባቸው እና አሁንም እየተወዳደሩ ከሚገኙ አትሌቶች ጋር ሁሌም ቅራኔ አለኝ" ሲል አውስትራሊያዊው አትሌት ተናግሮ ነበር።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሆርተን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ጣሊያናዊ ጋር ግን ፈገግታ በተሞላበት መልኩ ፎቶግራፍ አብሮ ሲነሳ ታይቷል።

ሱን ለሚነሳበት ቅሬታ ምላሽ ሲሰጥ "ስለእኔ የሚባለውን እሰማለሁ። ልምምዴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" በማለት ብዙ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል።

አውስትራሊያዊው አትሌት በወሰደው እርምጃ የውግዘትም ሆነ የድጋፍ መልዕክቶች እየጎረፉለት ነው።

ሱን ከአበረታች ዕጽ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ምረመራዎች እየተካሄዱበት ይገኛል።

ተያያዥ ርዕሶች