እስራኤል በፍልስጤም ይዞታ ሥር የሚገኙ ቤቶችን እያፈረሰች ነው

እስራኤል በፍልስጤም ይዞታ ስር የሚገኙ 'በሕገ-ወጥ መንገድ ተገነቡ' ያለቻቸውን ቤቶች እያፈረሰች ነው Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ እስራኤል በፍልስጤም ይዞታ ስር የሚገኙ 'በሕገ-ወጥ መንገድ ተገነቡ' ያለቻቸውን ቤቶች እያፈረሰች ነው

እስራኤል በፍልስጤም ይዞታ ስር የሚገኙ እና ''በሕገ-ወጥ መንገድ'' ተገነቡ ያለቻቸውን ቤቶች ማፍረስ ጀመረች።

እስራኤል ''በሕገ-ወጥ" ተገነቡ የምትላቸው ቤቶች እአአ 1967 በተካሄደው የስድስት ቀን ጦርነት ከተቆጣጠረቻቸው ግዛቶች አንዱ በሆነው ዌስት ባንክ አጥር አቅራቢያ የተገነቡ ቤቶችን ነው።

በፖሊስ እና በእስራኤል ጦር የታጀቡ ቡልዶዘሮች እነዚህን መኖሪያ ቤቶች ሲያፈራርሱ ታይተዋል።

ነዋሪዎች ቤቶቹን ለመገንባት ከፍልስጤም ግዛት አስተዳደር ኃላፊዎች ፍቃድ ማግኘታቸውን እና እስራኤል ቤቶቹን የምታፍርሰው የዌስት ባንክ መሬትን ለመውረር ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

እየሩሳሌም፡ የትራምፕን ውሳኔ ዓለም እያወገዘው ነው

አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእሥራኤል መዲናነት እውቅና ልትሰጥ ነው

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን ቤቶቹ የተገነቡበት ቦታ ግንባታ ላለማካሄድ ስምምነት የተደረሰበት ሥፍራ ነው በማለት ቤቶቹ እንዲፈርሱ ድጋፉን ሰጥቷል።

ቤቶቹ የተገነቡት በፍልስጤም አስተዳደር ሥር በሚገኝ የዌስት ባንክ ግዛት ውስጥ እና እስራኤል በገነባችው ሁለቱን አካላት ከሚለየው አጥር መካከል ነው።

እስራኤል በዌስት ባንክ እና አቅራቢያው አጥር የገነባችው ሁለተኛ የፍልስጤማውያን ተቃውሞ ከተቀጣጠለ በኋላ ነበር። እስራኤል ግንቡ ከፍልስጤም አቅጣጫ ሊቃጣብኝ የሚችለውን የሽብር ጥቃት እና የደህንነት ስጋትን ለማስቀረት የገነባሁት ነው ትላለች።

ፍልስጤማውያን ግን የፍልስጤም ምድርን ለመውረር እና የዘር መድልዎ ለማድረግ ነው በማለት ግንቡን 'የአፓርታይድ ግንብ' ሲሉ ይጠሩታል።