የሱዳን አማጺ መሪ አዲስ አበባ ላይ እየተደረገ ካለ ድርድር ተይዘው ሊባረሩ እንደነበር ተነገረ

Sudan Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የሱዳን ፍትህና እኩልነት የተሰኘው ተቃዋሚ ቡድን መሪ የሆኑትን ጂብሪል ኢብራሂምን ከበርካታ ባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ሱዳን ተላልፈው ሊሰጡ ነበር።

በሱዳን ለተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት ዓላማ አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ድርድር አንድ የሱዳን አማጺ ቡድን መሪን አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሙከራ መደረጉ ተነገረ።

በዳርፉር ዋነኛው አማጺ ቡድን የሆነው የፍትህና እኩልነት እንቅስቃሴ መሪ የሆኑት ጂብሪል ኢብራሂም የተባሉት ግለሰብ ናቸው ተይዘው ከኢትዮጵያ እንዲባረሩ ሊደረግ የነበረው ተብሏል።

የኢትዮጵያን አደራዳሪነት የሱዳን ህዝብ እንዴት ይመለከተዋል?

የሱዳን አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ምንድነው?

ኦማር አል-በሽር ከወራት በኋላ ታዩ

ቢቢሲ ክስተቱን ለማጣርት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ነቢያት ጌታቸውን ያናገረ ሲሆን ቃል አቀባዩ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

በሱዳን ታጣቂ ቡድኖችና በተቃዋሚዎቹ ጸረ መንግሥት እንቅስቃሴ መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር የተጀመረው ሃገሪቱ ውስጥ ለወራት የዘለቀውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብቃት ያስችላል የተባለው ስምምነት በጊዜያዊው ወታደራዊ አስተዳደርና በተቃዋሚዎች መካከል ከተደረሰ ከቀናት በኋላ ነው።

ትናንት ዕሁድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ምንም ዓይነት መረጃ ሳይሰጡ የሱዳን ፍትህና እኩልነት የተሰኘው ተቃዋሚ ቡድን መሪ የሆኑትን ጂብሪል ኢብራሂምን ከበርካታ ባልደረቦቻቸው ጋር ነጥለው በመያዝ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ወስደዋቸው እንደነበር በድርድሩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ተቃዋሚዎቹ መካከል አንዱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪዎች በክስተቱ ውስጥ ጣልቃ ገብተው በድርድሩ ላይ መጥፎ ውጤት ሊኖረው ይችል የነበረውን የቃዋሚዎቹን ከአዲስ አበባ የማባረር ድርጊትን አስቁመውታል።

በሱዳን ያጋጠመውን ቀውስ ለመፍታት የአማጺ ቡድኑን ጨምሮ ሁሉም አካላት በወደፊቱ የሃገሪጡ እጣ ፈንታ ላይ መስማማት እንዳለባቸው ይታመናል።

በሱዳን ሠራዊት ጄነራሎችና በተቃውሞ እንቅስቃሴው መሪዎች መካከል ባለፈው ሳምንት የተደረሰው ሥልጣንን የመጋራት ስምምነት ረገድ ለውጦች ታይተዋል። ሆኖም ግን ዋነኛው ተቃዋሚ ኃይል የሆኑት የሱዳን አብዮታዊ ግንባር በስምምነቱ ባለመካተቱ ከሕዝቡ ጋር የሱዳንን የሰላም ጥረት ወደፊት ለማራመድ እነዚህ ተቃዋሚዎች የሚሳተፉበት ድርድር ለማደረግ ነው አዲስ አበባ ላይ የተገናኙት።