"አዲስ አበባ የምንወዛገብባት ሳትሆን በጋራ የምንኖርባት ከተማ ናት" ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

አዲስ አበባ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትሆን ከተማ በመሆኗ ለውዝግብና አለመግባባት ምክንያት መሆን እንደሌለባትና የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ ልናሳድጋት እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለቢቢሲ ተናገሩ።

አዲስ አበባ የሃገሪቱ እምብርት መሆኗን የሚጠቅሱት ምክትል ከንቲባው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫም መሆኗን ጠቅሰው "አዲስ አበባ ሁሉንም የምታቅፍ የሁሉም ከተማ ናት። ከተማዋ የመወዛገቢያ ርዕስ ሳትሆን ኢትዮጵያዊያን በጋራ የምንኖርባትና የምናሳድጋት ልትሆን ይገባል" ብለዋል።

የአዲስ አበባ መስተዳደርና የባላደራው ምክር ቤት

አስተዳደራቸው የከተማዋን ነዋሪ ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ እቅዶች እንዳሉት የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ በአዲስ አበባ ውሰጥ ያለው የቤት ችግር በከተማዋ ካሉ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለችግረኞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ በቤቶች ልማት በኩል ትልቅ የሚባል ተግባር አከናውኗል የሚሉት ምክትል ከንቲባው፤ የቤቶች ልማት ፕሮጀክትን በተመለከተ እስካሁን የነበረውን አሰራር በመለወጥ፣ በመንግሥት ሲከናወን የነበረውን የቤቶች ግንባታ የሪል እስቴት አልሚዎች እንዲገቡበት ይደረጋል ብለዋል።

ለዚህም "የከተማዋ አስተዳደር ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማዘጋጀት የተለያዩ የገንዘብ ተቋማት እንዲሳተፉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋል" ብለዋል።

በአዲስ አበባ ቢያንስ 3.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ትራንስፎርመሮች ተሰረቁ

በመጪው አዲስ ዓመትም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና ለመንግሥት ሰራተኞች በርካታ ቁጥር ያላቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ይጀመራል ያሉት ከንቲባው፤ ግንባታው የሚካሄደው እንደከዚህ ቀደሙ በመንግሥት ሳይሆን በግል ተቋማት ይሆንና መንግሥት የመቆጣጠርና የማስተባበር ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ተናግረዋል።

በከተማዋ ውስጥ የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ አሳሳቢ ከሆኑት ነገሮች መካከል የሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው "ስጋቱ ትክክለኛ ነው። ነገር ግን በግልጽ መናገርና ማረጋገጥ የምፈልገው በየትኛውም የኢንቨስትመት ሥራ ምክንያት ሰዎች አይፈናቀሉም" ብለዋል።

ለዚህም ባለፈው ዓመት የምክትል ከንቲባነት መንበሩን ሲረከቡ ቃል መግባታቸውን የሚያስታውሱት ከንቲባው "በመልሶ ማልማትና ከተማዋን ለማሳደግ ነዋሪውን እንደማናፈናቅል ለሕዝቡ ቃል ገብተናል። ከዚያ ይልቅ ነዋሪውን ማልማትና ልማቱንም እዚያው እናካሂዳለን" በማለት ነዋሪዎችን ከመሃል ከተማ በማንሳት ራቅ ያሉ አካባቢዎች ማስፈር እንደማይኖር ገልጸዋል።

ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በኦሮሚያ ተቃውሞን ቀሰቀሱ

ለገሃር አካባቢ የሚካሄደው ግንባታንም በተመለከተ ሲናገሩ በስፍራው ከሚከናወኑት ግዙፍ ግንባታዎች ጎን ለነዋሪው የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ ጠቅሰው፤ በዚህም ሳቢያ የግለሰቦች መፈናቀል እንደማይኖር ሲያስረዱ "ማረጋገጥ የምፈልገው በልማት ስም የትኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ አይፈናቀልም። ይህ ታሪክ በእርግጠኝነት ያለፈ ክስተት ነው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተጨማሪም የአዲስ አበባን ሰላም የተጠበቀና አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታና የደህንነት ጉዳይን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት እንደሆነ ጠቅሰው የከተማዋ የጸጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ውስጥ ሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለውን እገዳን በተመለከተም የተጠየቁት ም/ከንቲባው እዚህ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት በየአንዳንዱ ቀን አዲስ አበባ ውስጥ በሞተር ሳይክሎች አማካይነት ዝርፊያ ይፈጸም ነበር ብለው፤ በዚህ ምክንያትም ሞተር ሳይክሎች ላይ በተጠና መልኩ ክልከላ መጣሉን ይናገራሉ።

"ታከለ ኡማ አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም" እስክንድር ነጋ

እስካሁን የነበረው ሁኔታ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡትን ሞተር ሳይክሎች ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ነገሮች እንዳልነበሩና በዚህም ምክንያት ዝርፊያና የደህንነት ስጋት እንደተፈጠረ በመግለጽ "በቀጣይ ሞተር ሳይክሎቹ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ሕግና ደንብ ይዘጋጃል" ብለዋል።

የከተማው አስተዳደር ሞተር ሳይክሎች ላይ እገዳውን ከጣለበት ዕለት ጀምሮ "በሚያስደንቅ ሁኔታ በከተማዋ ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። ያጋጥሙ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ከግማሽ በላይ በሆነ ሁኔታ ለመቀነስ አስችሏል" ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

ስለሞተር ሳይክሎቹ ዝርዝር መረጃ እንኳን እንደሌለ እገዳውም ያሉት ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ እንደሚቆይ የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው አስፈላጊው ህጋዊ የቁጥጥር ሥርዓት ከተዘረጋ በኋላ ግን ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

ም/ከንቲባው አክለውም ሞተር ሳይክሎቹን የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ የጂፒኤስ ሥርዓት እንደሚዘረጋ አመልክተው፤ ከሚዘረጋው ሥርዓትና ደንብ ውጪ ማንም በከተማዋ ውስጥ እንዲሰራ አይፈቀድለትም ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ