ሳባ አንግላና፡ "ኢትዮጵያዊትም፣ ጣሊያናዊትም ሶማሊያዊትም ነኝ"

ሳባ አንግላና Image copyright Enrico Carpegna
አጭር የምስል መግለጫ ሳባ አንግላና

ሳባ አንግላና ከኢትዮጵያዊት እናቷና ከጣሊያናዊ አባቷ የተወለደችው ሞቃዲሾ ውስጥ ነው። የእናቷ ቤተሰቦች በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ነበር በምርኮኛነት ወደ ሶማሊያ የተወሰዱት። ከዓመታት በኋላ እናቷ አንድ ጣሊያናዊ ሞቃዲሾ ውስጥ ተዋወቀች፤ ትውውቃቸው ወደ ፍቅር፣ ፍቅራቸው ወደ ትዳር አደገ፤ ከዚያም ሳባ ተወለደች።

ስልጣን ላይ በነበረው በሞሐመድ ዚያድ ባሬ መንግሥት አስተዳደር ወቅት የሳባ እናትና አባት ሞቃዲሾ ውስጥ ተደላድለው መኖርና ልጃቸውንም ማሳደግ የማይታሰብ ሲሆንባቸው ያላቸውን ሸክፈው ወደ አባቷ ሀገር ጣሊያን አመሩ።

ሳባ የሦስት ሀገራት ነጸብራቅ በውስጧ በአንድ ላይ ይታይባታል። ስትጠየቅም ይህንኑ ታስረዳለች፤ በእናቷ ኢትዮጵያዊ፣ በአባቷ ጣሊያኒያዊ፣ እትብቷ የተቀበረው ደግሞ ሶማሊያ ውስጥ ቢሆንም ጥርሷን ነቅላ ያደገችው ግን ሮም ከተማ ውስጥ ነው።

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

ሳባ ለጥበብ ጥሪ 'አቤት' ብላ ምላሽ የሰጠችም ናት፤ ትወና ነፍሷ ነው፤ ደራሲና ድምፃዊም ናት።

"ሳባ ብለው የሰየሙኝ ንግሥቲቷን በማሰብ ነው ... ለእኔ ግን በስሜ ራሱ አንድ ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለበኝ ነው የማስበው" ትላለች።

Image copyright Enrico Carpegna
አጭር የምስል መግለጫ ሳባ የኢትዮጵያ የሃገር ባህል ልብስ ተውባ መድረክ ላይ ስታንጎራጉር

ሳባ "ብዙ ጊዜ ከአንድ ወይም ሁለት በላይ በባህል፣ በደምና በማንነት 'የተዳቀሉ' (ክልስ) ሰዎች ለየት ያለ እሳት በውስጣቸው እንደሚነድ አምናለሁ። ሆኖም ግን ነበልባሉ የሚተነፍስበትን ትክክለኛ መውጫ ማግኘት ያስፈልጋል" በማለት በውስጧ ስላለው ራሷን በሙዚቃ ለመግለፅ ስላላት ጽኑ ፍቅር ትናገራለች።

ሙዚቃን የሕይወት ጥሪዬ ነው ብላ የተቀበለችውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ስታስረዳ "በውስጤ የነበረውን ነበልባል የማወጣበት የሆነ ነገር ያስፈልገኝ ነበር" በማለት ነው።

ከልጅነቷ ጀምሮ እግሯ በረገጠበት ሁሉ ዜግነቷን ትጠየቅ ስለነበር፤ በሙሉ የራስ መተማመን መልስ ለመስጠት እንደትችል ማንነቷን ማወቅና መገንባት ነበረባት።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

"ሙዚቃ፤ ነፃነቴንና ተቃውሞዬን የምገልጽበት ቋንቋ ነው" የምትለው ሳባ ማንነቷን ራሷ እየገነባችው እንደመጣች ታስረዳለች።

ሳባ ወደ ሙዚቃው ዓለም የተቀላቀለችው እድሜዋ ሠላሳን ከዘለቀ በኋላ ነው። ለምን? ስትባልም አባቷን ታነሳለች።

"...በልጅነቴ ሁል ጊዜ አንጎራጉር ነበር። ነገር ግን ቤተሰቦቼ በተለይ አባቴ ሙዚቃው እንዳይስበኝ ይጥር ነበር" በማለት አባቷ ፊደል ቆጥራ፣ ተምራ፣ ተመራምራ የዕለት እንጀራዋን እንድታበስል ይመክሯት እንደነበር ትናገራለች።

አባቷ ካረፉ በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ፤ "አባቴ ቆንጆ ድምፅ እንዳለኝ ለሰው ሁሉ ይናገር እንደነበር ተነገረኝ። ውስጤ በጣም ደማ፤ ምክንያቱም ለእርሱ ባንጎራጉርለት ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር። ምነው ለራሴ በነገረኝ ኖሮ እያልኩ ወደ ሙዚቃው ተሳብኩ" ትላለች።

ኢትዮጵያዊት? ጣልያናዊት? ወይስ ሶማያዊት?

ሶማሊያ ተወልዳ ያደገችው ሳባ ለዚህ ጥያቄ መልሷ "ሦስቱም" የሚል ነው። የልጅነትና የወጣትነት እድሜዋን በሮም ብታሳልፍም በእናቷ በኩል ያለውን የዘር ግንዷን ለማወቅ ወደ አዲስ አበባ መጥታ የአያቶቿን መቃበር ጎብኝታለች።

"ሶማሊያዊያን ሶማሊያዊት ነሽ ይሉኛል፣ ኢትዮጵያውያንም ኢትዮጵያዊት ነሽ፤ ዓይኖችሽ ይናገራሉ ይሉኛል። ጣልያኖችም የራሳቸው ያደርጉኛል። እኔ ግን ሦስቱም ነኝ" ትላለች።

“እዚህ ደረጃ የደረስኩት በእርሷ ብርታት ነው” አርቲስት ደመረ ለገሰ

"በውስጤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘኝን ነገር ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር። አማርኛ አለመቻሌ ትልቅ ቁስል ፈጥሮብኛል ... በተለይ ኢትዮጵያን ስጎበኝ 'ፈረንጅ' እያሉ የሚከተሉኝ ልጆች የኢትዮጵያዊነቴን ስሜት የተገፈፈኩ ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል" የምትለው ሳባ የማንነቷን ፍለጋ ጉዞዋ በሙዚቃ በኩል እንደተያያዘችው ታስረዳለች።

ከድምፃዊት ቤቲ ጂ እና ቸሊና ጀርባ

Image copyright Enrico Carpegna
አጭር የምስል መግለጫ ሳባ አንግላና

"አበበች"

አበበች የሳባ ሙዚቃ አልበም መጠሪያ ነው። ነገር ግን ወ/ሮ አበበች ወደ ሳባ ሕይወት እንዲሁ የተከሰቱ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ሳይሆኑ አያቷ ናቸው። ከኢትዮጵያ ጋር በጥብቅ ገመድ ያስተሳሰሯት፤ የማነሽ? የከየት ነሽ? ጥያቄዎች መልሷ ናቸው።

"አያቴ አበበች ነበር ስሟ" ትላለች ሳባ ስለእርሳቸው ማስረዳት ስትጀምር፤ "በእርሷም በኩል ነው የኢትዮጵያዊነቴ ግንድ የተገለጠልኝ" በማለትም የመጨረሻውን የሙዚቃ አልበሟን በእዚሁ ምክንያት በእርሳቸው ስም "አበበች" ብላ እንደሰየመችው ትናገራለች።

ወ/ሮ አበበች ለአውሮፓያውያን ወግኖ በነበረ የሶማልያ ወታደር እንደ ምርኮኛ ወደ ሶማልያ ተወስደው እንደነበር ሳባ ትተቅሳለች።

"ስለእርሷ በሙዚቃዬ ማውራቴ ደግሞ ስሬ ምን ያህል ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የማመላክትበት ነው" ትላለች ሳባ። ሙዚቃዋን በኢትዮጵያ ፔንታቶኒክ ስኬል፣ በአምባሰልና በትዝታ ቅኝት የምትጫወትበትም ምክንያት ይኸው እንደሆነ ታስረዳለች።

አውታር - አዲስ የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ

በሙዚቃዋም በትዝታ ጎዳና በማንነትን ፍለጋ አቀበት እየተጓዘች፣ የሚያደምጧትንም ጭምር ጉዞዋን ተቀላቅለው አብረው እንዲነጉዱ ታደርጋለች። ሳባ አብዛኞቹ ሥራዎቿ እራስን ከመፈለግ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ማንነቷ በሙዚቃ ሥራዎቿ በግልጽ የሚንፀባረቀው ሳባ፣ በአራት የተለያዩ ቋንቋዎች ታንጎራጉራለች። ሶማልኛ፣ አማርኛ፣ ጣልያንኛና እንግሊዘኛ ሙዚቃዎቿን ያቀረበችባቸው ቋንቋዎች ናቸው። ይህን በማድረጓም ማንነቷን በደንብ እንደገለፀች ይሰማታል።

አራቱንም ቋንቋዎች እንደ ተወላጆቹ እንደልብ አፏ ላይ ባታሾራቸውም መኮላተፏ ግን የመሳሳቷ ሳይሆን የውህድ ማንነቷ ውጤት መሆኑን ትናገራለች።

"መኮላተፌም ሆነ መሳሳቴ ...የማንነቴ አካል ስለሆነ አላፍርበትም።"

'ኢትዮጵያዊነት' ከጄሰን ድሩሎ ጀርባ ያለው ቡድን

"የሁሉም ሰው ማንነት አንድ ነገር ብቻ ሊሆን አይችልም" የምትለው ሳባ በምዕራቡ ዓለም እየታዩ ያሉት ስደተኞችን ወደ ሀገራቱ እንዳይገቡ የመከላከል እርምጃን ታወግዛለች።

ምክንያቱስ ስትባል "ውበታችን የሚጎላው እንደዚያ ስለሆነ ነው" በማለት "ምንም ልዩነቶች ቢኖሩ የሰው ልጅ አንድ ነው" በማለት ሃሳቧን ታጠናክራለች።

መድረክ ላይ በምትሆንበት ጊዜ ፊት ለፊቷ ያለው ታዳሚዎች ኢትዮጵያዊም ሆኑ ጣልያናዊ አልያም ሶማሊያዊ መልዕክቷን ስለሚረዱ በጣም ዕድለኛ እንደሆነች ትገልፃለች።

"ምንጊዜም ችግር የሚገጥመኝ አንዱን ባህል ብቻ እንዳንፀባርቅ ሲጠብቁ ነው... ለምን? አንድ ነገር ብቻ አይደለሁም" በማለት በሁሉም የሙዚቃ ሥራዋ ሦስቱንም ቋንቋና ባህልን እያደባለቀች የምትሰራበት ምክንያቷን ታስረዳለች።

"ከእኔ በኋላ ለሚመጡት ሙዚቀኞች በር እንደከፈትኩ ያህል ይሰማኛል። ምክንያቱም መንፈሳዊነቴን፣ ባህሎቼንና ማንነቴን በአንድ ላይ በሙዚቃዬ ለመግለፅና ተቀባይነት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን አይቻለሁ። አሁን ግን የቅይጥነቱን መንፈስና ትርጉም ብዙዎች የተረዱት ይመስለኛል" የምትለው ሳባ የአቅሟን በመሥራት ለመጪው ትውልድ አሻራ ብቻ ሳይሆን መንገድ እንደምትጠርግም ተስፋ ታደርጋለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ