አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

አቶ ተመስገን ጥሩነህ Image copyright AMMA

ዛሬ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደድር ሆነው ተሹመዋል።

አቶ ተመስገን ከክልል እስከ ፌደራል በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ አገልግለዋል። በቅርቡም በሚንስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።

"አሁንም እያጣራን ማሰሩም፤ መፍታቱም ይቀጥላል" ኮሚሽነር አበረ

ስለ'መፈንቅለ መንግሥት' ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

በምስራቅ ጎጃም ብቸና የተወለዱት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ጎተራ እና ብቸና በላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል።

የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ በኮምፒዩተር ሳይንስ፤ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በአመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።

ከዚያም በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፤ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም ሠርተዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መስሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡

አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊም ነበሩ።

በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል- አቶ ተመስገን ጥሩነህ።

እስከ ዛሬ ሐምሌ 15/2011 ዓ.ም ድረስ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

አቶ ተመስገን ዛሬ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

አዴፓ እነ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን "የእናት ጡት ነካሾች" አለ

አቶ ተመስገን የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በሕግ እንዲመለሱ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንደሚተጉ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች ላይ ከቀደመው በበለጠ ትኩረት እንደሚያደርጉ፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለትምህርት ጥራት፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለኢንቨስትመንት እድገት፣ በሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ለምክር ቤቱ ቃል ገብተዋል።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ተፈፀመ በተባለው 'መፈንቅለ መንግሥት' የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ ሌሎች የአዴፓ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከተገደሉ አንድ ወር በኋላ ነው ሹመቱ የተካሄደው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ላቀ አያሌው ክልሉን በጊዜያዊነት ሲመሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ