ቻይና፡ በዕፅ ዝውውር የተጠረጠረችው ናዝራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረበች

ናዝራዊት አበራ Image copyright Facebook

እፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ ቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ናዝራዊት አበራ ከወር በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቧንና የመጨረሻውን ፍርድ እየተጠባበቁ እንደሆነ እህቷ ቤተልሔም አበራ ለቢቢሲ ገለፁ።

ናዝራዊት አበራ በቻይና በእፅ ዝውውር ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ከተሰማ ስድስት ወራቶች አልፈዋል።

“ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከደወሉልን በኋላ ተረጋግተናል” የናዝራዊት አበራ እህት

"ናዝራዊት አበራ ላይ ክስ አልተመሰረተም" የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

ታዲያ ባለፈው ወር ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበችው። 5.2 ኪሎ ግራም [ከዚህ ቀደም 1 ኪሎ ግራም የሚመዝን እፅ እንደነበር ገልፀውልን ነበር] የሚመዝነውን በሻምፖ መልክ የተያዘጋጀ ኮኬይን የተሰኘ እፅ ማን እንደሰጣትና እንዴት ልትያዝ እንደቻለች ለአገሪቱ ፍርድ ቤት አስረድታለች።

የቻይና መንግሥት ያቆመላት ጠበቃም ናዝራዊት ከአገር ወጥታ እንደማታውቅ የሚያሳይ የጉዞ ታሪክ ማስረጃ፣ ከወንጀል ነፃ መሆኗን፣ የትምህርቷንና የሥራዋን ሁኔታ -ኢንጂነር እንደሆነች የሚያመለክት ማስረጃ ማቅረቡን እህቷ ቤተልሔም አበራ ገልፀውልናል።

እህቷ ማስረጃዎቹ የቀረበባትን ክስ ለመከላከል የላኩት መሆኑን በመጥቀስ "የቻይና ሕግ ከባድ ሳይሆን አይቀርም፤ እንዳሰብነው እየሄደ አይደለም ግን ተስፋ አንቆርጥም" ብለዋል።

በሌላ በኩል አቃቤ ሕግ ሆነ ብላ ድርጊቱን እንደፈፀመችና የተማረች ሆና ሳለ በስህተት ይህን መቀበል አልነበረባትም ሲል ክሱን ማሰማቱን ነግረውናል።

"በድጋሚ መቼ ፍርድ ቤት እንደምትቀርብ ቁርጥ ያለ ቀን አይታወቅም" የሚሉት እህቷ ቤተልሔም፤ በቻይና ሕግ መሠረት አንድ ሰው ፍርድ ቤት ከቀረበ ከሃያ ቀናት አሊያም ከወር በኋላ የመጨረሻው ብይን እንደሚሰጥ መረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ።

በቻይና የተደረሱት ስምምነቶች የትኞቹ ናቸው?

በመሆኑም የናዝራዊትን የመጨረሻ ብይን በተስፋ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ነግረውናል።

እርሳቸው እንደሚሉት በእስር ላይ ያለችውን ናዝራዊትን በአካል መጎብኘት ባይቻልም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ልካላቸዋለች።

"መጀመሪያ አካባቢ የጉዳዩ ክብደት አልገባትም ነበር፤ እመጣለሁ ነበር የምትለው። አሁን ላይ ክብደቱም ገብቷት ጭንቀቷ ጨምሯል።" ሲሉ ናዝራዊት ስላለችበት ሁኔታ ያስረዳሉ።

በደብዳቤዋ ላይም 'የተሳሳተ ሰው በማመኔ ቤተሰቦቼንም እኔንም ብዙ መስዋዕትነት አስከፈልኩ፤ ወጥቼ አኮራችኋለሁ' የሚል ሃሳብ አስፍራለች።

እንደ ቤተሰብ አሁንም በወር የተወሰነ ገንዘብ እንደሚልኩላትና ቻይና ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችም በወር አንድ ጊዜ እንደሚጎበኟት፤ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም እንደሚሄዱ ገልፀውልናል።

በቻይና አንድ ሰው እፅ ሲያዘዋውር ከተገኘ የሞት ፍርድ እንዲበየንበት የሚያዘው ሕግ በናዝራዊት ላይ ተግባራዊ ይሆናል በሚል በቤተሰቦቿ፣ በቅርብ ዘመዶቿ እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ዘንድ ስጋትን አሳድሯል።

ጉዳዩንም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ መገለፁ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ