"በኤችአይቪ የምሞት መስሎኝ ልጄን ለጉዲፈቻ ሰጠሁ"

ከጀርባ የምትታይ ሴት

"2007 ዓ. ም አካባቢ ይመስለኛል. . . ልደታ አካአንድ ፈረንጅ ወንድ ልጅ ቅፎ አየሁ። ፈረንጁ የቤተሰብ ፎቶ እንጨት ላይ ይለጥፋል. . . ስልክ እየደወለሰዎች ጋር ያወራል. . . ያቀፈው ልጅ ቀላ ያለ ነው. . . ልጁን ትኩር ብዬ ሳየው ደነገጥኩ። ልጁ ልጄን ይመሰላል!

ሥራቸው ቆሜ ማልቀስ ጀመርኩ። ፈረንጁም ልጁም አማርኛ አይችሉም። ዝም ብዬ ሳለቅስ ግራ ሳይገባቸው አልቀረም።

'ዋት ኢት ኢዝ. . . ዋት ኢት ኢዝ' ምናምን አለኝ። ምን ብዬ ልመልስለት? ግራ ገባኝ። በቆምኩበት ማልቀሴን ቀጠልኩ።

በአካባቢው እያለፈ የነበረ ሰውዬ መጣና 'ምንድን ነው?' አለኝ። እየተጣደፍኩ 'ፈረንጁ ያቀፈው ልጅ ልጄን ይመስላል፤ በእናትህ ከየት እንደመጡ ጠይቅልኝ' አልኩት። በእንግሊዘኛ አወሩና። ፈረንጁ የልጁን [የጉዲፈቻ ልጅ] ቤተሰቦች ለመፈለግ ከእንግሊዝ እንደመጣ ነገረኝ።

ማልቀስ ማቆም አልቻልኩም. . . እንደገና ደግሞ መሳቅ ጀመርኩ. . . እንደ ሞኝ መንገድ ላይ ቆሜ ሰዎቹን ማየት ቀጠልኩ። አለቅሳለሁ. . . እስቃለሁ. . . አለቅሳለሁ. . . መልሼ ደግሞ እስቃለሁ።

ልጄን ሳፈላልግ የገጠመኝ ይሄ ብቻ አይደለም። የቱን ነግሬሽ የቱን እተወዋለሁ። ልጄ ይሆን? ብዬ ድንግጥ ያልኩት ብዙ ጊዜ ነው። ልደታ የገጠመኝን ግን መቼም መቼም አልረሳውም!"

"ልጄን ለምኜም ቢሆን አሳድገዋለሁ"

በላይነሽ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) ልጃቸውን ለጉዲፈቻ ከሰጡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እናቶች አንዷ ናት። ልጇ በማደጎ ወደ ካናዳ ከሄደ በኋላ አድራሻው ጠፍቶባት ለዓመታት በፍለጋ ባዝናለች።

መንገድ ላይ ከነጭ ጋር ያየችውን ጥቁር ልጅ 'የእኔ ይሆን?' ብላ መደንገጥ ካሳለፈችው መከራ ቀለል ያለው ነው።

ጉልበቷ ከድቷት መንገድ ላይ ተዝለፍልፋ የወደቀችባቸውን ቀናት ቆጥራ አትጨርስም። በሯን ዘግታ ያነባችውን በእሷና በጠባብ ቤቷ መካከል መተው ትመርጣለች።

እናትና አባቷ ከሞቱ ቆይተዋል። ክፍለ አገር የምትኖር አንድ እህት አለቻት። ግን በላይነሽ የት እንደምትኖር አታውቅም፤ አይጠያየቁምም። የቅርብ ዘመድ፣ ጓደኛም ከጎኗ የለም።

የመጀመሪያ ልጇን ከአንድ ወታደር የወለደችው ከ20 ዓመት በፊት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከወታደሩ ጋር ተለያዩ። ልጁም ለሩቅ ዘመድ ተሰጠ።

ያኔ በአስራዎቹ መጨረሻ ላይ የነበረችው በላይነሽ ከሌላ ወታደር ጋር ትዳር መስርታ ካምፕ ውስጥ መኖር ጀመረች። ሁለተኛ ልጇን አርግዛ በ1993 ዓ. ም ባለቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

'ጆሮ ለባለቤቱ . . . ' እንዲሉ ባለቤቷ በምን ምክንያት እንደሞተ አቃውቅም ነበር።

"ባለቤቴ በሽታው [ኤችአይቪ] እንዳለበት አላውቅም ነበር። ውትድርና ሄዶ ቆስሎ ነበር የመጣው። እንደዚህ አይነት ነገር መኖሩን ግን በጭራሽ አላውቅም ነበር። ሁሉንም ነገር ያወኩት ከወለድኩ በኋላ ነው። ለካ አንድ ጓደኛው ያውቅ ነበር። 'ልጁን አስወጪው' አለኝ። እንዴ ልጄን ለምን አስወርዳለሁ? ልጄ የሙት ልጅ ነው። ባሌም ልጁን ሳያይ ነው የሞተው። ልጄን ለምኜም ቢሆን አሳድገዋለሁ አልኩት።"

1994 ዓ. ም ሚያዝያ ላይ ልጇን ወለደች። ወዲያው ትኖርበት ከነበረው የወታደር ካምፕ እንድትወጣ ተደረገ። መጠለያ አልነበራትምና ቀበሌ ሄዳ ማልቀስ ጀመረች። ከብዙ ሄደት በኋላ አሁን የምትኖርበት አንድ ክፍል ቤት ተሰጣት።

የባሏን የጡረታ 100 ብር እየተቀበለች ኑሮን እየተንገታገተች ጀመረች። ሀብቷ ልጇ ነበርና እሱው ላይ አተኮረች። አንድ ዓመት ሲሞላው ልደቱን አከበረችለት።

አብረው ፎቶ ተነሱ. . . ደስ አላት።

ከልደቱ በኋላ ያማት ጀመር። ቀስ በቀስ ህመሙ ጸንቶባት መንቀሳቀስ ተሳናት።

"ሆስፒታል አልጋ ያዝኩ። በጉልኮስ ነበርኩ። ስታመም አንድም ሰው አጠገቤ አልነበረም።"

"ያ ጠባሳ ይኖር ይሆን?"

ሆስፒታል ተኝታ ልጇ አጠገቧ ድክ ድክ ይል ነበር። የሚጠብቀው ሰው ስላልነበረ አሁንም አሁንም ይወድቅ ነበር። ልጇን ከወደቀበት የማንሳት አቅም አልነበራትም እንጂ።

አንድ ቀን ወድቆ ክፉኛ ተጎዳ። ያኔ ግንባሩ ቆስሎ እንደነበር ታስታውሳለች። ቁስሉ ዛሬ ከ18 ዓመታት በኋላ ግንባሩ ላይ ይኑር ይጥፋ አታውቅም። ያ ጠባሳ ይኖር ይሆን?. . . ታስባለች።

የልጇ ምልክት፣ የቀደመ ሕይወቱ ማስታወሻ ጠባሳው ይሆናል. . .

ሰው ቤት ያደገው የመጀመሪያ ልጇን አዘውትሮ የማየት እድል አልነበራትም። አንድ ጊዜ ብቻ ታናሽ ወንድሙ የአምስት ወር ልጅ ሳለ አይቶት ነበር።

ህመሙ በላይነሽን ከእለት ወደ እለት እያዳከማት ሄደ።

"በቃ አትተርፊም ተባልኩ። እንደምሞት ሲነግሩኝ ልጄን ማን ያሳድገዋል? ብዬ ፈራሁ። ልጅሽን ለጉዲፈቻ ስጪ ሲሉኝ ባንገራግርም በወቅቱ ተስፋ ቆርጬ ነበር። ከጉዲፈቻ ውጪ አማራጭ እንደሌለኝ አሰብኩ። ሞቼ እስክቀበር ድረስ እንኳን ልጄን የሚይዝልኝ ሰው ስለሌለኝ በማደጎ ለመስጠት ወሰንኩ።"

አዲስ አባበ ውስጥ ከሚገኝ የጉዲፈቻ ድርጅት ጋር ተነጋገረች። እዚያው ሆስፒታል ሆና ልጇን ወሰዱት።

ልጇ ወደ ድርጅቱ ከተወሰደ በኋላ የእናት አንጀቷ አልችል አላት። እየተንገዳገደች ከሆስፒታል አልጋ፣ ወርዳ ታክሲ ተኮናትራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልጇን በድርጅቱ ጊቢ ውስጥ አየችው። ተሰናብታው ሞቷን ወደምትጠባበቅበት አልጋ ተመለሰች።

"አልቅሼ አልቅሼ አልቅሼ ተመለስኩ፤ ምን ላድርግ? ተስፋ ቆርጬ ነው እንጂ ከልጄ መለየትስ አልፈለኩም ነበር።"

1996 ዓ. ም ላይ ሳትሰማ ሳታይ ካናዳዊያን ጥንዶች የአንድ ዓመት ከስምንት ወልጇን በማደጎ ወሰዱት።

"አንቺ ልትሞቺ ነው፤ ለምን የልጅሽን እድል ትዘጊያለሽ?"

ሆስፒታል ሳለች ህመም፣ ሀዘን፣ ሰው ማጣት እንደተደራረበባት ታስታውሳለች።

አንድ ሴት 'የአገሬ ልጅ ነሽ' ብላ ምግብ የምትሠራላትና የምታስታምማት ሠራተኛ ቀጥራላት ነበር። በመጠኑ ማገገም ጀመረች።

ያኔም ዛሬም ልጇን በጉዲፈቻ ለመስጠት የወሰነችበትን ቅጽበት ደጋግማ ታስባለች። ልክ ነበርኩ? ስህተት ሠርቼ ይሆን? መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች።

ልጇን ለመስጠት ስታቅማማ 'አንቺ ልትሞቺ ነው፤ አትተርፊም፤ ለምን የልጅሽን እድል ትዘጊያለሽ?' ተብላለች። የድርጅቱ ሠራተኞች ሊያግባቡዋት፣ ሊያሳምኗትም ይሞክሩ ነበር።

"ልጄን ለማደጎ ሊሰጡ ሲሉ በጣም ፈርቼ ነበር። ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? እኔ ከሞትኩ ማን ያሳድገዋል? ሀኪሞቹም ሳይቀሩ አትተርፊም አሉኝ። መቆም አልችል፣ የምሄደው ተደግፌ. . . ልጄ ከሄደ በኋላ የቲቢ መድሀኒት መውሰድ ጀመርኩ። መድሀኒቱን ስጨርስ ፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት መውሰድ ጀመርኩ። ከዚያ ቀስ በቀስ ጤናዬ እየተሻሻለ መጣ። በፍጹም ባልጠበቅኩት ሁኔታ ሳልሞት ቀረሁ። በስተመጨረሻም ከሆስፒታል ወጥቼ ቤት ገባሁ።"

ኦና ቤት ተቀበላት። እንቅልፍ አጣች። አልጋዋን ስትዳብስ ልጇ አጠገቧ አለመኖሩን መቀበል አልቻለችም። 'ከሞት ተርፌ ልጄን እፈልጋለሁ' ብላ አስባ አታውቅም።

የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት እየወሰደች ብታገግምም አዕምሯዋ አልረጋጋ አለ። ለሁለት ዓመት ቀን ከሌሊት አነባች።

"በጣም የተሰማኝ ከሀኪም ቤት ወጥቼ ቤቴ ስገባ ነው። እንዲህ ተሽሎኝ ቤቴ ልገባ ነው ልጄን የሰጠሁት? ጡት እንዳታጠቢው [ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ እናቶች እንዳያጠቡ ይመከራሉ] ስለተባለ አላጠባሁትም። ያደገው በወተትና በአጥሚት መሆኑን ሳስብ በጣም አዝንለታለሁ።"

ልጇን ለጉዲፈቻ ወደ ሰጠው ድርጅት ሄዳ 'የልጄን አድራሻ ስጡኝ' ብላ ጠየቀች። ልጇ ሲወስዱ ለእሷ 'አሳቢ' የመሰሏት ሰዎች ተለውጠው እንደጠበቋት ትናገራለች።

የድርጅቱ ሠራተኞች አንዳቸው ወደ ሌላቸው ይመሯት ጀመር። በሄደች ቁጥር በተለያየ መንገድ እምቢታቸውን ይገልጹላታል።

'ለምን አተይውም? 18 ዓመት ሲሞላው ይመጣል'

'ልጅሽን ፈቅደሽ ከሰጠሽ በኋላ አሁን አምጡ ማለት ምን ይባላል?'

'በቃ አሳልፈሽ ሰጥተሽዋል፤ አሁን ሌላ ቤተሰብ አለው!'

ብዙ የሚያሳምሙ መልሶች ተሰጧት።

"አንዷ የድርጅቱ ሠራተኛ ስደውልላት 'በሽታሽ ነው የሚያቃዥሽ?' ያለችኝን አልረሳውም። በየቀኑ ያስለቅሱኝ ነበር። ይሰድቡኝ ነበር። ካናዳ ያለው ኤጀንሲ ተዘግቷል ብለውኝ አልቅሼ፣ አዙሮኝ ወድቄያለሁ። ለዓመታት ከተመላለስኩ በኋላ ተስፋ ቆርጬ ቀረሁ።"

በወቅቱ ያገኘቻት አንድ ነርስ ልጇን ለማደጎ በመስጠቷ እንዳትፀፀት ትመክራት እንደነበር ታስታውሳለች። ልጇ ውጪ አገር በመሄዱ የተሻለ ትምህርት ሊያገኝ፣ የተሻለ ሕይወት ሊገጥመው እንደሚችልም ልታሳያት ትሞክር ነበር።

"እሷም እኔም ልጆቻችንን እየፈለግን ነበር"

በላይነሽ ፍርድ ቤት ውስጥ የፅዳት ሠራተኛ ናት። ብቸኛ ብትሆንም የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት እየወሰደች፣ ራሷን እየተንከባከበች ኑሮ ቀጠለች።

ዘወትር የሚያቃጭለው የልጄ የት ደረሰ? ጥያቄ እረፍት ይነሳታል። ልጄ 'ለምን ለሰው ሰጠችኝ?' ብሎ ይጠላኝ ይሆን ብላ ትሰጋለች። አንዳዴም 'እነሱስ ወይ እስከምሞት ወይ እስከምተርፍ ድረስ ልጄን ቢይዙልኝ ኖሮ ምናለ?' ትላለች።

ልጇን በሰጠው ድርጅት ተስፋ ስትቆርጥ ወደ ካናዳ ኤምባሲ መመላለስ ጀመረች። 'ውጪ ጉዳይ ጠይቂ' ተባለች። ውጪ ጉዳይ 'እስኪ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሂጂ' አሏት። የሦስቱ ተቋሞች ባለ ጉዳይ መሆን እንዳሰበችው አልጠቀማትም።

አንዱ ከሌላው 'ደብዳቤ አምጪ' ሲላት. . . ሌላው 'የሚመለከተውን አካል ጠይቂ'. . .

"ሁሉም ሲያመናጭቁኝና ሲያስለቅሱኝ ተውኳቸው። መመላለሱ ሰለቸኝ፤ ደከመኝ። ፀሀይ ሲመታኝ ያዞረኛል፤ መንገድ ስሄድ እግሬን ያመኛል። አንድ ቀን በጣም ተሰማኝና ብቻዬን መንገድ ላይ ቁጭ ብዬ አለቀስኩ።"

ውጪ አገር የሄዱ ልጆች ወላጆቻቸውን ለማግኘት እንዳይጓጉ ለቤተሰቦቻቸው አድራሻ አይሰጥም ብትባልም ልጇ ካናዳ ካሉት አሳዳጊዎቹ ጋር የተነሳው ፎቶግራፍ 'ሪፖርት' ተብሎ እንደቀረበላት ትናገራለች።

ከዚያ በዘለለ ስለ ልጇ አታውቅም።

ከሁለት ዓመት በፊት ፍርድ ቤት መደበኛ ሥራዋ ላይ ሳለች ከአንድ ሴት ጋር ጨዋታ ጀመሩ።

ሴቲቷ እንደ በላይነሽ ሁሉ ልጇ በጉዲፈቻ ካናዳ ከሄደ በኋላ ልታገኘው እንዳልቻለች ነገረቻት። የበላይነሽና የሴቲቷ ልጅ ለማደጎ የሰጠው ድርጅት ተመሳሳይ ነው። ልጁ የተሰጠው እናትና አባቱ ሞተዋል ተብሎ ነበር። እናቱ ልጁን መፈለግ ስትጀምር 'ቤተሰቡ ሞቷል ብለናል ስለዚህ ልናገናኝሽ አንችልም' የሚል መልስ ተሰጣት።

ሴቲቷ 'ቤተሰብ ፍለጋ' የሚባል ድርጅት ልጇን እያፈላለገላት እንደሆነም ለበላይነሽ አጫወተቻት።

ቤተሰብ ፍለጋ ከኢትዮጵያ በማደጎ የተወሰዱ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር የሚያገናኝ ድርጅት ነው። ልጁን የሚፈልግ ቤተሰብ፤ ልጁ በጉዲፈቻ ስለተሰጠበት ሂደት የሚያውቀውን መረጃ ይሰጣል።

የልጁ ስም፣ ፎቶ፣ የወሰደው ድርጅት፣ የሄደበት አገር. . . ልጁን ለማፈላለግ የሚረዳ ማንኛውም መረጃ ይመዘገባል። ቤተሰብ ፍለጋን የመሰረተችው አሜሪካዊት አንድርያ ኬሊ መረጃውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመልቀቅ ልጁን ወይም የልጁን አሳዳጊዎች ትፈልጋለች።

የተስፋ ጭላንጭል የታያት በላይነሽ ስለ ልጇ ያላትን መረጃ ለአንድርያ አስተላለፈች።

እጇ ላይ ልጇን ለማደጎ ከሰጠው ድርጅት የወሰደችው የልጇና የአሳዳጊ ቤተሰቦቹ ፎቶና ስም ነበር። ልጇና እሷ የተነሱት ፎቶ፣ 'የህጻኑ እናት በህመም ምክንያት ልጁ ለጉዲፈቻ እንዲሰጥ ፍቃደኛ ነች' የሚል የፍርድ ቤት ደብዳቤም ነበራት።

መረጃው በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቆ በጉጉት እየተጠባበቀች ሳለ፤ ከወደ ቶሮንቶ መልካም ዜና ተላከላት።

የልጇ አሳዳጊ ቤተሰቦች ተገኙ።

"ፎቶውንስ አየሁት፤ በአይነ ሥጋ የምንገናኘው መቼ ይሆን?"

የበላይነሽ ልጅ አሳዳጊዎች የተገኙት ፌስቡክ ላይ ነበር። ካናዳ፣ ቶሮንቶ ይኖራሉ። የጉዲፈቻ ልጃቸው ወላጅ እናት ልጇን እየፈለገች መሆኑ ሲነገራቸው አባትየው የልጁን ፎቶ ሊልክላት እንደሚፈልግ ገለጸ።

"አንድ ቀን ከአንድርያ ጋር የምትሠራ ልጅ ቤቴ መጣች። ልጄን የሚያሳድገው ሰው በቫይበር የላከላትን ፎቶ ይዛ። ሳየው እንዴት ደስ እንዳለኝ ልነግርሽ አልችልም። 17 ዓመቱን ጨርሶ 18ኛውን ይዟል። እኔ ያወጣሁለትን ስም ቢቀይሩትም አሁን የሚጠራበት ስም እኔ ከሰጠሁት ጋር ይቀራረባል። ቤተሰቦቹ 'አይዞሽ፤ ልጁ ጥሩ ነው፤ ትምህርትም ጎበዝ ነው' ብለውኛል። በጣም እንደሚወዱት፤ እንደሚንከባከቡትም ነግረውኛል።"

ቤተሰቡ ልጁ ስላለበት ሁኔታ ለእሷ ለመንገርና ፎቶውን ለማሳየት ቢስማማም በአካል እንድታገኘው ፍቃደኛ ስለመሆናቸው አታውቅም። ለልጇ ወላጅ እናቱ እየፈለገችው እንደሆነ ይንገሩት አይንገሩትም እርግጠኛም አይደለችም።

የልጇን ፎቶ ማየት የሰጣት እፎይታ 'ልጄን በአይነ ሥጋ የማየው መቼ ነው?' የሚለው ጥያቄ እንዳጠላበት ትናገራለች።

"ልጄን የያዙበት መንገድ ደስ ብሎኛል። ጥሩ እድገት ላይ ነው። ሰዎቹን ባላያቸውም በጣም ጥሩ ሰዎች ይመስሉኛል።ይህን ያህል ፍንጭ ማግኘቴ ራሱ ተስፋ ይሰጠኛል።እግዚአብሔር ፍቃዱ ሆኖ ይን ለይን ብንተያይ በጣም ደስ ይለኛል። በይኔ ባየው. . . ባቅፈው. . . ብስመው. . . እመኛለሁ።

ልጄ በሕይወት ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር። አየዋለሁ ብዬ ገምቼም አላውቅም ነበር። አንድ ቀን እንምንገናኝ ተስፋ ማድረግ የጀመርኩት አሁን ነው፤ ፎቶውን ሳየው።ሱ ምክንያት ውስጤ በጣም ተጎድቷል። አንዴ እንኳን ልቀፈው እንጂ ሌላማ ምን ላለሁ?. . . መድሀኒቴን በትክክል እየወሰድኩ ነውቤት ያፈራውን እየቀመስኩ።እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ!

አኗኗሬ ግን በጣም ያስጠላል። ብቸኛ ነኝ። በዚች ቀበሌ በሰጠኝ ቆርቆሮ ቤት የምኖረው ምኑ ይወራል? ብርዱ፣ ጭቃው. . . በዚህ ላይ ደሞ የኑሮ ውድነት አለ. . . አንዳንዴ ባልኖር ይሻላል እላለሁ. . . ግን ልጄን ሳላይ ለምን ልሙት?