መገደል፣ መደፈር፣ መዘረፍ ማብቂያ የሌለው የኢትዮጵያውያን የስደት ጉዞ

ኡመር ሰዒድ
አጭር የምስል መግለጫ ኡመር ሰዒድ የ16 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ወደ ሳዑዲ አረቢያ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰደደው

"የሞተ ሰው ሲቀበር አይቻለሁ። ሴቶች ሲደፈሩም አይቻለሁ። ምንም ማድረግ ስለማንችል አልቅሰን ትተናቸው ነው የምናልፈው" የምትለው ዘምዘም ሃሰን ናት።

ይህ ዞን መዳረሻቸውን አረብ አገር ለሚያደርጉ ሰዎች የስቃይና ሰቆቃ ምናልባትም የሞትና መደፈር መነሻ ነው። ለሕገ ወጥ ደላሎች ደግሞ ይህ ዞን ኪሳቸውን የሚሞሉበት ሥፍራ ነው።

ይህ ዞን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነው።

በሶማሊያ፣ በጅቡቲ እና በሱዳን በኩል አድርገው መዳረሻቸውን መካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጉ ስደተኞች ይህንን ዞን በየምሽቱ ይሰናበታሉ።

የትኞቹ ሃገራት ከፍተኛ ስደተኛ አላቸው?

"ቀን የምንቀሳቀስ ከሆነ ልንያዝ ስለምንችል ሁልጊዜ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት እስከ ሱቢ ሶላት ድረስ ብቻ ነው የምንጓዘው" ትላለች ከአንድም ሁለቴ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የተሰደደችው ዘምዘም።በስደት ላይ የሚደርስባቸው ስቃይ ያማረራቸው ወጣቶች በቃን ብለው ወደ ቀያቸው ሲመለሱ፤ ሌሎች ደግሞ የስደት ጉዞ ይጀምራሉ።

ድህነትእና ሰቆቃ. . .

ወጣት ኡመር ሰኢድ የ16 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር ጂሌ ዱጉማ ከምትባል ወረዳ በመነሳት የስደት ጉዞ የጀመረው።

"አንድ አረብ ማድረግ ያስጠለውን ነገር ቢያዝህ፤ እምቢ ማለት አትችልም፤ የተባልከውን ታደርጋለህ" ይላል።

ከዓለም አቀፉ የስደተኖች ድርጅት (IOM) ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ድርጅቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 እና 2019 ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 2500 ወጣቶችን ወደ ኢትዮጵያ መልሷል።

ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የተሰደደው ኡመር፤ በስደት ላይ የደረሰባቸውን በደል ሲያስብ እምባውን መቆጣጠር አይችልም።

"እስከ ቦሳሶ ሱማሊያ ድረስ በእግር ነው የተጓዝነው። ቦሳሶ እስክንደርስ ከፍተኛ ስቃይ ነው የደረሰብን። በቢላዋ አስፈራርተው የለበስነው ልብስ እንኳ ሳይቀር ዘርፈውናል። የምንበላው እያጣን፤ ብዙ ጊዜ ሕይወታችንን ያተረፍነው ምግብ በመለመን ነው" ይላል።

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

ኡመር ቤተሰቦቹ አቅመ ደካማ ስለሆኑ ትምህርቱን ከ8ኛ ክፍል ለማቋረጥ መገደዱንና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ቢሰደድም ከየመን መመለሱን ይናገራል።

ኡመር እንደሚለው ታናሽ ወንድሙም ለደላሎች 20ሺህ ብር ከከፍለ በኋላ ከስንት ውጣ ውረድ ሳዑዲ ቢደርስም ያለ ሥራ እንዲሁ ተቀምጦ ይገኛል።

አቶ አንተነህ ፍቃዱ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሠራተኛ ስምሪት፣ የአሠሪና ሠራተኛ አስተዳደር ክፍል ውስጥ ባለሙያ ናቸው።

ከድህንነት በተጨማሪ በማህብረሰቡ ውስጥ ያለው የተሳሳተ አመለካከት፤ በዞኑ ውስጥ በስፋት ለሚታየው የሕገ ወጥ ስደት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

በራዊ ቀውስ . . .

አቶ አንተነህ በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ማኅበራዊ ቀውስ ወጣቶች ሕገ ወጥ ስደተን እንደ አማራጭ እንዲወስዱ ያስገድዳቸዋል ይላሉ። በዞኑ ሕጋዊ መንገድ ተከትለው ከአገር ከሚወጡት በሕገ ወጥ መንገድ ጉዞ የሚጀምሩ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

የተመዘገቡ አሃዞች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በሕገ ወጥ መንገድ ከዞኑ ተሰደው የነበሩ ከ11ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሰዋል።

አቶ አንተነህ እንደሚናገሩት፤ ከተመላሾቹ መካከል ቀላል የማይባለውን ቁጥር የሚይዙት፤ የአካል ጉዳትና የአእምሮ ጤና ቀውስ አጋጥሟቸው የተመለሱ ናቸው።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

ሌላ ተስፋ . . .

አጭር የምስል መግለጫ ዘምዘም ሃሰን

ኡመር ሰኢድ ለሁለት ዓመታት የመን ቆይቶ ተመልሷል። ኡመር እንደሚለው አሁንም ቢሆን ወደዚያው ለመሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

በአረብ አገር ያስፈልገኛል ብሎ ያሰበውን ክህሎት ለመቅሰም፤ በከሚሴ ከተማ በአንድ ተቋም ውስጥ ለህጻናትና እርዳታ ለሚሹ ሰዎች እንክብካቤ እንዴት እንደሚደረግ ስልጠና እየወሰደ ይገኛል።

"አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው"- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

"በሕገ ወጥ መንገድ የስደት ጉዞ ማድረግ እጅግ አደገኛ ነው። እኔ በጣም ጠልቼዋለሁ። ሌሎች ሰዎችም የሕገ ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ መምረጥ የለባቸውም" የምትለው ዘምዘም ሃሰን፤ 12 ዓመታትን በስደት አረብ ሃገር ቆይታ አሁን በከሚሴ ከተማ ኑሮዋን መስረታለች።

"በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይሄዱ ብዙዎችን እመክራለሁ። እነሱ ግን አይሰሙኝም" ትላለች ዘምዘም።

በዞኑ የስደት ተመላሾችን ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት አስተኛ መሆኑን መታዘብ ችላናል።

የዞኑ ሠረተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ ወደ አረብ አገራት ጉዞ ሚያደርጉ ወጣቶች ሕጋዊ መንገዶችን እንዲመርጡ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ይናገራል።