ጋላክሲ ፎልድ የ’ስክሪን’ መሰበር ችግሩ ’’ተቀርፎ” ለገበየ ዝግጁ ሆኗል

ሳምሰንግ ፎልድ

የመጀመሪያው ታጣፊ የሆነው ስልክ የ'ስክሪን' መሰበር ችግር ለገበያ እንዳይቀርብ ካዘገየው በኋላ መስከረም ወር ላይ ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ የሳምሰንግ ኩባንያ አስታውቋል።

ከሶስት ወራት በፊት የሳምሰንግ ታጣፊ ስልክን ቀድመው የሸመቱ ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ 'ስክሪኑ' እየተሰበረብን ነው የሚል ቅሬታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ኩባንያው የስልኩን የምርቃት ጊዜ አዘግይቶት ነበር።

አንዳንድ ሸማቾች ስልኩ ላይ ያለው 'ስክሪን' ስልኩን ከአደጋ እንዲከላከል የተቀመጠ መስሏቸው የስልኩን 'ስክሪን' መገንጠላቸው ደግሞ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ሳምሰንግ እንደ መጽሐፍ የሚገለጥ ስልክ አመረተ

ታጣፊው የሳምሰንግ ስልክ የ'ስክሪን' መሰበር ወቀሳ ቀረበበት

ኩባንያው 'የችግሩ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ስልኩ እንዲታጠፍ የሚረዳው ማጠፊያ ነውና እሱን እናስተካክል ዘንድ ጥቂት ሳምንታት ስጡን' ብሎ ነበር።

ወደ 60ሺህ ብር ገደማ ዋጋ የተቆረጠለት ሳምሰንግ ፎልድ በተመረጡ ገበያዎች ብቻ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ እና አስፈላጊ ማሻሻያዎች እንደተደረጉለት ኩባንያው አስታውቋል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ "ሳምሰንግ ጊዜ ወስዶ አዲሱን ምርት መርምሯል፣ ከበርካታ ፍተሻ በኋላ አስፈላጊውን ማስተካከያዎች አድርጓል" ይላል።

ሳምሰንግ ከተፎካካሪዎቹ ቀድሞ ታጣፊ ስልክ ለማስተዋወቅ ሲጥር ቆይቷል።

የሳምሰንግ ተፎካካሪ ከሆኑት ግንባር ቀደም ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ሁዋዌ ከሁለት ወራት በኋላ የራሱን ታጣፊ ስልክ ለማስተዋወቅ ቀነ ቀጠሮ ይዟል።

ሁዋዌ በዓለማችን በርካታ ሞባይሎችን በመሸጥ ሁለተኛ ደረጃን ተቆናጥጧል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዢዮሚ የሚሰኘው የቻይና ስልክ አምራች ኩባንያ ወደ ታብሌት የሚቀየር የስልክ ዲዛይን አቅርቦ ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ