በእነብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ለሀምሌ 29 ተቀጠሩ

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ Image copyright FACEBOOK

ሰኔ 15 በአማራ ክልል ተሞከረ ከተባለው 'መፈንቅለ መንግስት' ጋር በተያያዘ የጸጥታ ኃላፊዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩና በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ጉዳይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ታይቷል።

ፖሊስ በአጠቃላይ የ90 ሰዎችን ቃል መስማቱን ገልጾ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማስፈለጉን በምክንያትነት አስቀምጧል።

"እናቴ ካልመጣች አልመረቅም" ኢዛና ሐዲስ ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

በእለቱ ጥቃት የደረሰባቸውና ጥቃቱን ለመመከት የሠሩ መኖራቸውን እና ማስረጃ የሚያስቀርብ በቂ ፍንጭ አለመኖሩን በመጥቀስ የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የጊዜ ቀጠሮውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ከወንጀሉ ጋር የሚያያዝ ምንም ፍንጭ እንዳልተገኘባቸው የገለጹት ኮሎኔል አለበል አማረ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። "ድርጊቱን ያስቆምኩት እኔ ነኝ" ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ በበከሉላቸው ምንም ማስረጃ ስላልተገኘባቸው የጊዜ ቀጠሮውን ፍርድ ቤቱ አንዳይቀበል ጠይቀዋል።

ሌሎች ተጠርጣሪዎችም የጊዜ ቀጠሮው ውድቅ እንዲሆን ጠይቀዋል። ከወንጀሉ አፈጻጸም አንጻር ጊዜ እንደሚያስፈልግ የገለጸው ፖሊስ በበኩሉ የሰው እና የቴክኒክ መረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል ብሏል።

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤት የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታታሉ ለሐምሌ 29/2011 ቀጠሮ ሰጥቷል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 218 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው መታየት ከጀመረ በኋላ 103 መፈታታቸው ይታወቃል። ከዛሬው ችሎት በኋላ ደግሞ 57 ይለቀቃሉ ተብሏል።

የሚለቀቁት ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ግን የተገለጸ ነገር የለም።ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በሰጠው መሠረት ህክምና እንዳላገኙ የገለጹ ሲሆን ፖሊስ ግን ህክምና እያገኙ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና እስያ ሠራተኞችን ልትልክ ነው

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት እንዲከናወን ብሏል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ ደሞዝ ማግኘታቸውን የጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ደሞዝ ያልተከፈላቸው እንዲከፈላቸው በጠየቁት መሠረት እንዲፈጸም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ማረሚያ ቤት መሄድ የሚፈልጉ እና በፖሊስ ጣቢያ መቆየት የሚፈልጉ በመኖራቸው ተለይተው እንዲቀርቡም ተጠይቋል።

በተጠርጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ስሜ ለሁለተኛ ቀን አልተጠራም ሲል አንድ ተጠርጣሪ የጠየቀ ቢሆንም ስሙ መኖሩን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል።

ለጋዜጠኞች ብቻ ክፍት በነበረው ሂደት ከተጠርጣሪዎች ብዛት አንጻር ክፍሉ ተጣቦ ነበር።በፍርድ ቤቱ እና በአካባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች