በተቃዋሚዎች ግድያ የሱዳን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

በካርቱም ግንቦት 26 የተገደሉትን ለማሰብ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት ተካሂዷል። Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በካርቱም ግንቦት 26 የተገደሉትን ለማሰብ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

ግንቦት 26 በሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ ከተፈጸመው ግዳያ ጋር በተያያዘ በ8 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ክስ ሊመሰረት መሆኑ ተነገረ።

የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደስታወቀው፤ በሱዳን መዲና ለተቃውሞ ወጥተው የተገደሉ የ87 ሰዎች አሟሟትን መርምሮ ከጨረሰ በኋላ ነው በከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ክስ እንደሚመሰርት ይፋ ያደረገው።

መንግሥት ግንቦት 26 ላይ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 87 ነው ይበል እንጂ ተቃዋሚ የመብት ተከራካሪዎች ግን የሟቾቹን ቁጥር 130 ያደርሱታል።

ዛሬ በሱዳን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 13 ደረሰ

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር አስተላልፎ ይስጥ በማለት ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ የመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ነበር በርካታዎቹ በአንድ ቀን የተገደሉት።

የጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ምረመራ ብዙዎችን እንዳላስደሰተ እና ለሌላ ተቃውሞ ሰዎች ወደ አደባባይ እንዲወጡ ጥሪ እየቀረበ መሆኑ በስፋት እየተዘገበ ነው።

በቅርቡ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱ እና ተቃዋሚዎች ስልጣን ለመጋራት ከተስማሙ በኋላ በተደረሰው ስምምነት መሰረት አዲስ መንግሥት ከተመሰረተ በኋላ ግድያውን የሚያጣራ ገለልተኛ ምረመራ ይካሄዳል።

በወታደራዊ ምክር ቤቱና በተቃዋሚዎች ጥምረት የሲቪል መንግሥት ለመመስረት በተደረሰው ስምምነት፤ ወታደራዊ ምክር ቤቱ በሕግ አውጪው ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ መቀመጫ ይኖረዋል።

በሱዳን ወታደራዊ ሕግ መሰረት፤ ኢሰብዓዊ ወንጀሎች በሞት ያስጣሉ።

በሱዳን ወታደራዊ ምክርቤቱና ተቃዋሚዎች ተስማሙ

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አደረኩት ባለው ምረመራ ስምንት የጦር መኮንኖች ለግድያዎቹ ተጠያቂዎች ናቸው ቢልም፤ የተጠርጣሪዎቹን ማንነት ግን ይፋ አላደረገም። የምርመራ ቡድኑ ሊቀ መንበር ፋት አል-ራሃማን ሰዒድ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ሦስት የጦር አለቆች ተቃዋሚዎች ተሰብስበው ወደ ነበረበት የመከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ጸጥታ አስከባሪዎችን በማሰማራት ሕግን ተላልፈዋል ብለዋል።

"ሕግን ተላልፈው ተቃዋሚዎቹ የተቀመጡበት ስፍራ ደረሱ። መተላለፊያዎችን ለመዝጋት የተጠቀሙበትን ቁሳቁስ አፈረሱ። አስቃሽ ጭስና ጥይቶችን በብዛት ተኮሱ። ይህም በርካቶች እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ፋት አል-ራሃማን ሰዒድ።

የምርመራ ቡድኑ በተወሰደው እርምጃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 87 እንዲሁም እንደሆነና ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ 168 እንደሆኑ አመልክቷል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ