ኦሳ ማዕከሉን በአዲስ አበባ እንዲከፍት ምክትል ከንቲባው ጠየቁ

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የኦሮሞ ጥናት ማህበር ጉባኤ ላይ (ኦሳ) ዛሬ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ማህበሩ ማዕከሉን አዲስ አበባ ላይ እንዲያደርግና ከዚህ በኋላ ዝግጅቱን ለማካሄድ ወደ ባዕድ ሃገር መመልከት የለበትም ብለዋል።

ከአርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የማህበሩ ጉባኤ የመጨረሻ ቀን ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባው፤ ማህበሩ ላለፉት 33 ዓመታት ሥራውን ለማከናወን ሲል መስዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱን ተናግረው፤ አሁን ግን ወደ ሃገር ቤት በመምጣቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም ማህበሩ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸውን ጥናቶች የፖሊሲና መመሪያዎች መሰረት መሆን ስላለባቸው በተቀናጀ መልክ በማዘጋጀት ለትውልድና ለሃገር በሚጠቅም መልኩ ሥራ ላይ እንዲውሉ መድረግ አለበት ብለዋል።

የኦሳ 33ኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀመረ

"መስዕትነት ስትከፍሉላቸው የነበሩ ጥናቶቻችሁን ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ በማየት ትውልድ፣ ሃገርና ሃብታችን ላይ ልዩነትን እንዲያማጣ ማድረግ ይጠበቅባችሏል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላም የኦሮሞ ጥናት ማህበር ሥራውን ለማከናወን ወደ ሌሎች ሃገራት ማየት እንደሌለበት የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው በአዲስ አበባ ከተማ ማዕከሉን ከፍቶ እንዲሰራ ጥሪም አቅርበዋል።

ማህበሩ ከዚህ በፊት ጥናቶቹን ያካሂድባቸው የነበሩትን መንገዶችን በአግባቡ ቀርጾና መዝግቦ የሚቀጥለው ትውልድ ውጤታማ ምርምር እንዲያደርግ መርዳት አለበት ሲሉ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ እንደ ሃገርና እንደ ግለሰብም ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

ምክትል ከንቲባው በተጨማሪም ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ በገዳ ሥርዓት ጥናት ላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ "ቤተሰቦቻችን ዋጋ ከፍለው ባያስተምሩን ኖሮ ዛሬ በዚህ መልኩ አንወያይም ነበር" ያሉት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የትምህርትንና የምርምርን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በጉባኤው የማብቂያ ዕለት ተገኝው ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባው የኦሮሞ ጥናት ማህበር ጉባኤ ተሳታፊዎች እየተካሄደ ባለው የችግኝ መትከል ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ችግኝ የመትከያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ጉባኤተኞቹም በችግኝ ተከላው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።