ናይጄሪያ ውስጥ ታግተው የቆዩ ቱርካዊያን ተለቀቁ

አራቱ ቱርካዊያን ታጋቾች Image copyright AFP

በናይጄሪያዋ ምዕራባዊ ግዛት ክዋራ ውስጥ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት የቱርክ ዜጎች ከሳምንት እገታ በኋላ መለቀቃቸው ፖሊስ ገለጸ።

የግንባታ ሰራተኞች የሆኑት አራቱ ቱርካዊያን ከአንድ ቡና ቤት የታገቱት ባለፈው ሳምንት ነበር።

ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን ለመልቀቅ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፤ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" ምንም ገንዘብ ሳይከፈል መለቀቃቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቀረቡ

ናይጄሪያ ውስጥ የውጭ ዜጎችና ታዋቂ የሃገሪቱን ዜጎች ኢላማ ያደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚና የተለመዱ ናቸው።

ከሁለት ሳምንታት በፊትም የባህር ላይ ዘራፊዎች ከናይጄሪያ የባህር ዳርቻ ዋ ብሎ አንዲት የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመው አስር ቱርካዊያን መርከበኞችን አግተዋል። የታጋቾቹ እጣ ፈንታም እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

የክዋሬ ግዛት የፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት ካዮዴ ኢግቤቶኩን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቱርካዊያኑ የግንባታ ሰራተኞች አርብ ዕለት ነው ጫካ ውስጥ የተገኙት።

ታጋቾቹን የማስለቀቅ ተልዕኮ በግዛቲቱ ፖሊሶች፣ በአካባቢው ታጣቂዎችና ከዋና ከተማዋ አቡጃ በተላኩ የፖሊስ መኮንኖች ጥምረት ነበር የተካሄደው።

መገደል፣ መደፈር፣ መዘረፍ ማብቂያ የሌለው የኢትዮጵያውያን የስደት ጉዞ

የግዛቲቱ ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉት ታጋቾቹ ከመገኘታቸው በፊት ፖሊስ የያዛቸው ሦስት አጋቾች ቱርካዊያኑን ለማስለቀቅ እንደረዱ ተናግረዋል።

"አጋቾቹ ሲያዙ በተቀሩት ተባባሪዎቻቸው ላይ ተጽእኖ በመፍጠሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ታጋቾቹን እንዲለቁ አድርጓቸዋል" በማለት ፖሊስ ሌሎቹን አጋቾች ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

አራቱ ቱርካዊያን ታጋቾች ከተለቀቁ በኋላ የህክምና ምርመራ ተደርጎላቸዋል። በናይጄሪያ የሚገኙት የቱርክ አምባሳደርም እገታው ያለጉዳት በማብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸው ተልዕኮው የተሳተፉትን በሙሉ ማመስገናቸው ተዘግቧል።

ተያያዥ ርዕሶች