ፓምፋሎን፡ የኢትዮጵያ ቦብ ማርሌ?

ፓምፋሎን Image copyright PAMFALON

የሁለት ሰዎችን ሕይወት የሚተርክ በልጆች መጽሐፍ ውስጥ ያለ ታሪክ ነው። አንደኛው ገፀ-ባሕሪ መንፈሳዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዓለማዊ ነበር።

መንፈሳዊው ከሰዎች እና ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ለሠላሳ ዓመታት ከፈጣሪው ጋር በመወያየት ቆየ። አንድ ቀን ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ ለመንፈሳዊው ግለሰብ ፈጣሪ ይገለጥለትና ወደ ፓምፋሎን እንዲሄድ ይነግረዋል።

ይህም ሰው ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቹ እንዴት ወደ ፓምፋሎን እንደተላከ ሊገባው አልቻለምና ፈጣሪውን "ለምን ወደ እርሱ ትልከኛለህ?" ብሎ ሲጠይቅ "በሰዎች ዓይን ፓምፋሎን ዓለማዊ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጅ መንፈሳዊነት በልቡ ያለ እንጂ በሰዎች የሚታይ አይደለም" ብሎ ይመልስለታል። "እኔም ለዚያ ነው የሙዚቃ ስሜን ፓምፋሎን ያልኩት" ይላል ፓምፋሎን።

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

የፓምፋሎን ተረት በሩስያዊ ደራሲ የተፃፈ ቢሆንም ፓምፋሎን ግን ከልጅነቱ ጀምሮ በጀርመን ሃገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ነው። ያለ እናትና አባት ያደገው ፓምፋሎን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ ነው ራሱን ማስተዳደር የጀመረው።

ስለ ሕይወት ታሪኩ እና ወደ ጀርመን እንዴት እንደሄደ ሲጠየቅ "እሱን ሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ ለሕዝብ ለማቅረብ ስለምፈልግ ለጊዜው ስለ ታሪኬ ለመናገር ዝግጁ አይደለሁም" ይላል።

በየወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ የሚለው ፓምፋሎን ነገሮች ቢመቻቹለት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያደርግ ይወዳል። ለጊዜው በሙዚቃ ስሙ ብቻ እንዲታወቅ እንደሚፈልግ ይናገራል።

Image copyright PAMFALON

ወደ ሙዚቃ የገባው በተለያዩ ነገሮች ተገፋፍቶ ነበር። "የተለያዩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የምጠቀምበት ስለሆነ ነው ሙዚቃ መሥራት የጀመርኩት። ጥበበኛ ነኝ ወይም ችሎታ አለኝ ማለትም አልፈልግም ምክንያቱም ለጊዜው ሙዚቃውን መልዕክት ማስተላለፊያ ነው ያደረግኩት" በማለት በትሕትና ይናገራል።

ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።

ኒኪ ሚናጅ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አልዘፍንም አለች

"ለጊዜው የሙዚቃ ዓለሙን ተቀላቀልኩ እንጂ ወደፊት ሌሎች ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት አለኝ" የሚለው ፓምፋሎን በሙዚቃዎቹ የተለያዩ ሰዎችን ንግግሮች ያካትታል። ከእነዚህም መካከል የማንዴላ፣ የማልኮም ኤክስ እና የዶ/ር ዐብይ አሕመድ ይገኙበታል።

ለምን ብሎ ሲጠየቅም በአንድ ወቅት ንግግሮቹ ስሜቱን ከነኩት የሙዚቃውን መንፈስ ለአድማጮቹ ለማስተላለፍ እንደሚያስችሉት በማሰብ እንደሆነ ይናገራል።

ገቢው በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ እንዳልተመሰረት የሚናገረው ፓምፋሎን "ሙዚቃዬ እያበላኝ አይደለም። የምተዳደረው በግራፊክ ዲዛይን፣ ፎቶግራፎችን በመሸጥ እና ሌሎች ነገሮች በመሥራት ነው" ይላል።

የሕይወቱን ሦስት አራተኛ በጀርመን ስለኖረ አልፎ አልፎ በጀርመንኛ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ይቀለዋል። ሆኖም ግን በአማርኛ ነው አልበሙን የሠራው። "ቋንቋ እንደአጠቃቀማችን ነው እና ጀርመንኛው ቀለል ይለኛል ግን ሆን ብዬ በሃገሬ ቋንቋ ነው ሙዚቃዬን የምሠራው ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ" በማለት ፓምፋሎን ይናገራል።

አክሎም "በልጅነቴ የተለያዩ የራፕ ቡድኖችን ተቀላቅዬ በጀርመንኛ ራፕ አደርግ ነበር። ሳድግ ግን ምንድነው ማድረግ የምፈልገው ብዬ አሰብኩበት። መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ማስተላለፍ እንደሆነ ሳውቅ በአማርኛ መሥራት ጀመርኩኝ" ይላል።

ታዋቂዎቹ ኤርትራዊያን በሙዚቃቸው ምክንያት ይቅርታ ጠየቁ

የሚሠራቸውን የተለያዩ የጥብብ ስራዎች በእኩል እንደሚመለከት የሚጠቅሰው ፓምፋሎን ቢገደድ እንኳን አንዱን ብቻ ለመመረጥ በጣም እንደሚከብደው የሚናገረው በመግለጽ እየሳቀ "ከሙዚቃውና ከፎቶግራፍ ምረጥ የሚለኝን ሰው እንደጠላት ነው የምቆጥረው" በማለት ይናገራል።

"የግጥም አፃፃፌ እራሱ ከኢትዮጵያ ገጣሚያን የተለየ ነው። ብዙዎችም ለየት እንደሚል ይነግሩኛል" በማለት በሃገሩ ቋንቋ ሥራዎቹን ለሕዝብ ማቅረብ መቻሉ እንደሚያስደስተው ይገልፃል።

"ለረዥም ዓመታት ከሃገር ውጪ እንደኖርኩኝ የሚያውቁ ሰዎች አማርኛዬን ሲሰሙ በጣም ይደነቃሉ። እኔም ብሆን ስሜቴን በእናቴ ቋንቋ መግለፅ በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ" የሚለው ፓምፋሎን ሙዚቃው በኢትዮጵያ ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር።

Image copyright PAMFALON

የፓምፋሎን ሙዚቃዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆች እንደልብ ይገኛሉ። እርሱም ዋናው ዓላማ በሙዚቃው ሰው ሊሰማው ይገባል ብሎ ያሰበውን መልዕክት እንዲተላለፍ መሆኑን ይናገራል።

ወጣት እያለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ የራፕ ሙዚቃ አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚያምነውን 'አፋሪስ' የተሰኘ የራፕ ቡድን አቋቁመዋል። አልበምም እስከ ማሳተም ደርሰውም ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ሞክረው ብዙም እንዳልተሳካላቸው ይጠቅሳል።

"በጊዜው ምናልባት ራፕ አልተለመደም ነበር ወይም የሕዝቡ ጆሮ አልተቀበለው ይሆናል፤ ቢያንስ መልዕክታችን በከፊልም ቢሆን ተሰምቷል" የሚል እምነት ያለው ፓምፋሎን ጓደኞቹ ፊታቸውን ወደ ቤተሰብ ሲያዞሩ "እኔ ግን ማይክሮፎኑን አልለቅም ብያለሁ" ይላል።

'ኢትዮጵያዊነት' ከጄሰን ድሩሎ ጀርባ ያለው ቡድን

ራፕ እንደሌላው የሙዚቃ ስልት እንዳልሆነ የሚናገረው ፓምፋሎን ሙዚቃው እና መልዕክቱ ከሩቅ ቦታ ሳይሆን ከእራስ የሚመጣ እንደሆነም ያስረዳል። ማንኛውም ራፕ የሚያደርግ ሰው በውስጡ የሚሽከረከሩ ሃሳቦችንና በሕይወታቸው ከሚያዩት እንደሚነሱም ይጠቅሳል።

"ብዙ ሰዎች ሥራዬን ላይረዱት ይችላሉ። እኔ ግን እራሴን የምገልፅበት ስለሆነ አያሳስበኝም። የሚረዳኝ ሰው ግን ማዳመጡ አይቀርም" በማለት ሙዚቃ በሕይወቱ ውስጥ የሚጫወተውን ትልቅ ሚና ይናገራል።

በሙዚቃው ደግሞ የሕይወት ታሪኩን ለሌሎች ማካፈል መቻሉ ሌሎችንም ሊረዳ ይችላል ብሎ እንደሚያስብ ይገልጻል።

የኢትዮጵያው ቦብ ማርሌ ቢባል ማጋነን ይሆን? ተብሎ የተጠየቀው ፓምፋሎን "በእራሴ ካላመንኩኝ ማን ያምንብኛል። እንደ ቦብ ማርሌ ነኝ ለማለት በጣም ይከብደኛል ትልቅም ክብር ነው። ነገር ግን ልክ እንደ ቦብ ማርሌ ሙዚቃዬ ከትውልድ ትውልድ መልዕክቱን እንዳዘለ ቢሰማልኝ ደስታውን አልችለውም" ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ