አምባሳደር ሬድዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለምን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አላቀረቡም?

አምባሳደር ሬድዋ Image copyright Anadolu Agency
አጭር የምስል መግለጫ አምባሳደር ሬድዋን

በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት የአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የሹመት ደብዳቤ እስካሁን በኤርትራ መንግሥት ተቀባይነት አላገኝም በሚል ወጣው መረጃ ትክክል አይደለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባብሏል።

ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከአንድ ዓመት በፊት በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሬድዋን ሁሴን የሹመት ደብዳቤያቸው በኤርትራ መንግሥት ተቀባይነትን አላገኝም የሚለው ዜና በስፋት መነጋገሪያ ነበር።

የኢፌድሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው "የአንድ አምባሳደር የሹመት ደብዳቤ በተቀባዩ ሃገር ተቀባይነትን አላገኘም የሚባለው፤ አምባሳደሩ በተቀባዩ ሃገር እንዲሰራ ሳይፈቀድለት ሲቀር ነው። አምባሳደር ሬድዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ በሶስተኛው ቀን ለኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አቅርበዋል። በዚህም መሰረት ስራቸውን እየሰሩ ይገኛል። አንድ አምባሳደር በተቀባዩ ሃገር ተቀባይነትን ሳያገኝ ሥራ መጀመር አይችልም" ሲሉ ያስረዳሉ።

ነገር ግን ዋናውን የሹመት ደብዳቤያቸውን እስከ አሁንም ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር አለማቅረባቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ

''የኤርትራ ኢኮኖሚያዊ ዕቅድ የተነደፈው በኢትዮጵያ ሃብት ላይ ነበር'' አምባሳደር አውዓሎም ወልዱ

''ዋናው ቅጂ (የሹመት ደብዳቤ) የሚቀርበው ለርዕሰ ብሔሩ ነው። ተቀባዩ ሃገር በሚያዘጋጀው መረሃግብር ላይ ደብዳቤው ለርዕሰ ብሔሩ ይቀርባል። እስከዛው ግን ለውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የሹመት ደብዳቤውን እስካቀረበ ድረስ አምባሳደሩ ስራውን ይሰራል። የአምባሳደር ሬድዋንም ከዚህ የተለየ ነገር አይደለም" በማለት አቶ ነብያት ያብራራሉ።

አምባሳደር አብደላ አደም በሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ነበሩ። አንድ አምባሳደር ወደ ተሾመበት ሃገር ከመሄዱ ከሶስት ወራት በፊት የሹመት ደብዳቤው ወደ ተቀባዩ ሃገር የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቢሮ ይላካል ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ አንድ አምባሳደር በተቀባዩ ሃገር ቀድሞውኑ ተቀባይነትን ሳያገኝ በምንም አይነት መልኩ ሹመቱ ወደ ተሰጠበት ሃገር ሊሄድና ሊሰራ አይችልም።

ይሁን እንጂ ይላሉ አምባሳደር አብደላ፤ "አንድ አምባሳደር የሹመት ደብዳቤውን ርዕሰ ብሔሩ ጋር ቀርቦ ካላጸደቀ፤ በተሾመበት ሃገር ከሚገኙ ሌሎች አምባሳደሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ላይ ትንሸም ቢሆን አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል'' ይላሉ።

አቶ ነብያት ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ የሌሎች ሃገራት አምባሳደርን እንደ ምሳሌ ሲያስረዱ፤ በኢትዮጵያ የበርካታ ሃገራት ኤምባሲዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ጽ/ቤት በሚያዘጋጃቸው ሥነ-ስርዓቶች የሹመት ደብዳቤዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግረው፤ እስከዚያው ግን ለውጪ ጉዳይ ደብዳቤያቸውን እስካስገቡ ድረስ ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

አቶ ነብያት በአሥመራ ይህን መሰል አይነት ፕሮግራም በቅርብ አለመካሄዱን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከሾመቻቸው አምባሳደሮች መካከል የሹመት ደብዳቤያቸውን ለየሃገራቱ ርዕሰ ብሄሮች ያላቀረቡ ሌሎች አምባሳደሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር። ቀደም ሲል በአየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚንስትር እንዲሁም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል።