የፓኪስታን የጦር አውሮፕላን ተከስክሶ 17 ሰዎች ሞቱ

ወታደሮችና ሌሎች ሠራተኞች አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ቦታ በሥራ ላይ Image copyright AFP

በፓኪስታን ራዋልፒንዲ ከተማ አነስተኛ የጦር አውሮፕላን በመኖሪያ ሠፈር ላይ ተከስክሶ 17 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ አደጋ መከላከል ባለሥልጣን አስታወቀ።

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

በአደጋው አምስት የበረራ ሠራተኞች፣12 ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን፤ እንዲሁም ሌላ 12 ሠዎች ጉዳት እንዳጋጠማቸው የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል። ከአደጋው የተረፈም የለም።

በበረራ ልምምድ ላይ እንደነበር የተነገረው አውሮፕላኑ በመከስከሱ ምክንያት በተፈጠረው እሳትም በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል።

የአደጋው ምክንያት ያልታወቀ ሲሆን አውሮፕላኑ የፓኪስታን ጦር አቪየሽን አካል ነው ተብሏል።

አደጋው በተከሰተበት የመኖሪያ መንደር አካባቢ በርካታ ሰዎች መሰብሰባቸውንና የሰዎች ለቅሶ እንደነበርም ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ጋዜጠኛ እንደተናገረው እስካሁን በአካባቢው ጭስ እንደሚታይና የአውሮፕላኑ ስብርባሪ በአቅራቢያው በሚገኝ ቤት ጣሪያ ላይ እንደተመለከተ አክሏል።

"የፍንዳታ ድምፅ ስሰማ ከእንቅልፌ ነቃሁ" የሚለው መሃመድ ሳዲቅ የተባለው ነዋሪ በወቅቱ ሰዎች እየጮኹ እንደነበርና እሳቱ ከፍተኛ ስለነበር እርዳታ ለማድረግ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

«ሙሉ ቤተሰቤን በኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ አጥቻለሁ»

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ በበኩሉ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት በእሳት መያያዝ እንደጀመረ ገልጿል።

በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ አቅራቢያ የምትገኘው ራዋልፒንዲ የአገሪቱ ጦር ዋና መሥሪያ ቤት መገኛ ነች።

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በግል አየር መንገድ ሥር የሚሰራ አውሮፕላን በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ ተከስክሶ ተሳፍረው የነበሩ 152 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።

ይህም በፓኪስታን ታሪክ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት አደጋ መሆኑ አይዘነጋም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ