በኢትዮጵያ በአንድ ቀን የተተከሉት ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንዴት ተቆጠሩ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ችግኝ ሲተክሉ

ትናንት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 'አረንጓዴ አሻራ' በሚል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ ተክለዋል። ይህንን ቀን በማስመልከት በአንዳንድ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም ባሉበት አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን መስበር እንዲሁም በአጠቃላይ 4 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ዓላማ ይዞ የተነሳ ነው።

በዚህ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአንድ ጀምበር ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በሕንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን ኢትዮጵያ መስበሯ ተዘግቧል። ለመሆኑ የተተከሉት ችግኞች እንዴት ተቆጠሩ?

ይህንን ሂደት ሲከታተል የነበረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ሲሆን በሥሩም አንድ ቡድን ተቋቁሟል። ቡድኑ የችግኝ ተከላዎችን አቆጣጠራቸውንና ምዝገባቸውን የሚከታተል ነው።

ያነጋገርናቸው የዚህ ቡድን አስተባባሪ አቶ ኢምራን አቡበከር በትክክል መተከላቸውን ለመቆጣጠር ቀድሞ የተሠራ ሶፍት ዌር መኖሩን ይናገራሉ። እርሳቸውም ይህንን ሶፍት ዌር በመስራቱ ረገድ ሚና ነበራቸው።

ሶፍት ዌሩ በዛፍ መትከያ ቦታዎች ላይ የተከላውን ሂደት ለመቆጣጠር የተመደቡ ሰዎች ስልክ ላይ ብቻ የሚሠራ ሲሆን በአካል በመገኘት የቆጠሩትን ችግኝ ብዛት የሚያስተላልፉበት ሥርዓት አለው።

በዚህም መሠረት በተመደቡበት ቦታ ላይ ምን ያህል ችግኞች እንደተተከሉ ቁጥሩን ሲያስገቡ ሶፍት ዌሩ በተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱትን አሃዞች በማጠቃለል እየደመረ ውጤቱን ይሰጣል። በመጨረሻ ላይም በአጠቃላይ በመላዋ ሃገሪቱ የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ያሳውቃል- ሶፍት ዌሩ።

ከዚህም ባሻገር ሌሎች የመቆጣጠሪያ መንገዶችን እንደተጠቀሙና ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አቶ ኢክራም ገልፀውልናል።

ከዚህ ቀደምም የተለያዩ የችግኝ መትከል ዘመቻዎች መከናወናቸው ይታወቃል። ሆኖም ምን ያህሉ ፀደቁ? የሚለው ላይ ባለሙያዎች ጥያቄ ያነሳሉ። የለም ኢትዮጵያ አካባቢ ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ወርቁ ችግኝ ከመተከሉ በፊት ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ይጀምራሉ።

"መንግሥት ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ የተጠና ሥራ መስራት አለበት" የሚሉት አቶ ሞገስ ሰሞኑን ችግኞች በተተከሉባቸው ቦታዎች ላይ ሰዎች ግንዛቤው ሳይኖራቸው ቁጥር ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ መታዘባቸውን ነግረውናል።

"አተካከላቸው ሳይንሱ የሚፈልገው ዓይነት አይደለም፤ አንዳንዱ ተከልኩ ለማለት ያህል ጣል አድርጎ የሚመጣ አለ" ሲሉ በግድ የለሽነት ችግኝ እንደማይተከል ያስረዳሉ።

ችግኝ ያልተተከሉባቸው ቦታዎች እያሉ የተተከሉባቸው ቦታዎች ላይ መልሶ መትከልም ጠቃሚ እንዳልሆነ አቶ ሞገስ ያነሳሉ።

"በአንድ ጊዜ አገሪቱን በደን መሸፈን ይቻላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው" የሚሉት አቶ ሞገስ በደንብ በባለሙያዎች በተጠና መልኩ፣ እቅድ ተይዞ፣ ይህን ያህል እንተክላለን ተብሎ፣ ቦታው ተለይቶ፣ የችግኞቹ ዝርያ ታውቆ፣ ችግኙም በወቅቱ ተዘጋጅቶ ሊካሄድ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ።

እስካሁን በነበረው ልምድ ችግኞች ሲተከሉ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ናቸው? አይደሉም? ብሎ ለመወሰን የሚያስቸግር መሆኑን በመግለጽ የተገኘው ሁሉ ነው ሲተከል የቆየው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ችግኞች ለመትከል የተደረገውን ይህን እንቅስቃሴና ዘመቻ ሳያደንቁ አላለፉም።