ኬንያ ውስጥ ታየ የተባለው "ኢየሱስ" ማን ነው?

ማይክል ጆብ Image copyright Syńbâd Twitter

በተለምዶ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የለበሰ የአንድ ግለሰብ ፎቶና ቪዲዮ በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል። እርስዎስ አጋጥሞዎታል?

ይህ ግለሰብ ማን ነው? ምንስ ሲያደርግ ነበር?

ይህንን በተመለከተ ከተሰራጩት የማህበራዊ ሚዲያ በርካታ መልዕክቶች መካከል በአንዱ ላይ "ደቡብ አፍሪካዊው ፓስተር ወደሚሰብክበት ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመንግሥተ ሰማያት ጋብዞ እንዲያስተምር አደረገ" የሚለው በታዋቂ ሰዎች ጭምር ሲጋራ ቆይቷል።

ነገር ግን ይህ የሆነው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሳይሆን ኬንያ ውስጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው። የወጡት ምስሎች ኪሴሪያን ተብላ በምትጠራው ከመዲናዋ ናይሮቢ በደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎ ሜትሮች እርቃት በምትገኝ ስፍራ የተገኙ ናቸው።

ይህ ምስሉ በስፋት እየተሰራጨና እያነጋገረ የሚገኘው ግለሰብ ማይክል ጆብ የተባለ አሜሪካዊ ሰባኪና የፊልም ተዋናይ ሲሆን፤ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ግብዣዎች ይቀርቡለታል።

እራሱን "ህያው የመጽሐፍ ቅዱስ ሙዚየም" ብሎ የሚጠራው እና ነዋሪነቱን ኦርላንዶ ፍሎሪዳ ያደረገው ጆብ፤ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ 'ዘ ሆሊላንድ ኤክስፒሪያንስ' በሚባል ፊልም ላይ ተውኗል።

ቀብር አስፈጻሚዎች ከሞት አስነሳሁ ያለውን ፓስተር ሊከሱ ነው

በደቡብ ኢትዮጵያ አጥማቂው በአዞ ተገደሉ

ግለሰቡ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ባወጣው ቪዲዮ ኬንያ ውስጥ ያሉ የግብርናና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ሱቆች የሚታዩ ሲሆን፤ ነገሩ የተከሰተው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደሆነ የሚገልጹት የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶችም ላይ ተመሳሳይ ነገር ይታያል።

ከዚህ ምስል ጋር በተያያዘ እየተዘዋወሩ የሚገኙት በርካቶቹ የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶችም 'አፍሪካ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰባኪያን እንዴት እያደረጉ ተአምራትን እናደርጋለን እንደሚሉ ያሳያል' በማለት አስፍረዋል።

ይህንን ምስል በመጠቀም የተሰራጨ አንድ ጽሁፍም "ኬንያዊው ፓስተር እየሱስ ክርስቶስን በኬንያ ጎዳናዎች ላይ አገኘሁት ይላል" ሲል አስፍሯል።

በትዊተር ላይ እየተዘዋወረ ያለው ፎቶም ማይክል ጆብ ኪቴንጌላ በተባለች ከተማ ውስጥ በሚገኝ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ሲሰብክ የተነሳው ነው።

በምሥራቅ ወለጋ የአራት ቀን ሬሳ አስነሳለሁ ብሎ መቃብር ያስቆፈረው 'ነብይ' በቁጥጥር ሥር ዋለ

በአንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ኬንያ ውስጥ በተቀረጸው ቪዲዮ አሜሪካዊው ግለሰብ ተአምራትንና ፈውስን እንደሚፈጽም ሲናገር ይታያል። በዚህም በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ትችቶች ቀርበውበታል።

ግለሰቡ አፍሪካ ውስጥ ጉብኝት ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ከወራት በፊት ወደ ቶጎ ሄዶ የነበረ ሲሆን እዚያ የተነሳቸው ፎቶግራፎች ግን ኮትና ሱሪ ለብሶ ስለነበረ የአሁኑን ያህል አነጋጋሪ አልነበረም።