የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አፍሪካዊያንን 'ዝንጀሮ' ማለታቸው ተጋለጠ

ሮናልድ ሬጋን Image copyright Getty Images

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን የካሊፎርኒያ ግዛት ሃገረ ገዢ በነበሩበት ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የአፍሪካ ተወካዮችንን "ዝንጀሮ" ሲሉ አንቋሸው እንደነበር ይፋ የሆነ አንድ የድምጽ ቅጂ አጋለጠ።

ዘ አትላንቲክ የተባለው መጽሔት የድምጽ ቅጂውን መሰረት አድርጎ ባወጣው መረጃ ላይ ሃገረ ገዢ የነበሩት ሬጋን የስልክ ጥሪዎቻቸውን በሙሉ በመቅዳት ከሚታወቁት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ጋር በስልክ ሲያወሩ ነበር ዘረኛ የሆነውን አገላለጽ የተጠቀሙት።

በቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ በሰው 800 ሚሊየን ዶላር ተጠየቀ

ሬጋን ይህ አፍሪካዊያንን የገለጹበትን መንገድ የተጠቀሙት በወቅቱ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ሃገራት ተወካዮች ዩናይትድ ስቴትስን በመቃወም ለቻይና እውቅና ሰጥተው ታይዋን ከድርጅቱ እንድትወጣ ድምጻቸውን በመስጠታቸው ነው።

በወቅቱ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ የታንዛንያ ተወካዮች በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ደስታቸውን በዳንስ ይገልጹ እንደነበር ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ በነበረው ቀን ሬጋን ወደ ፕሬዝዳንት ኒክሰን ደውለው የድምጽ አሰሳጡን በቴሌቪዥን ተከታትለውት እንደሆነ ጠይቀዋቸው ነበር።

በድምጽ ቅጂው ላይ ሬጋን አስከትለው "እነዚያ ከአፍሪካ ሃገራት የመጡትን ዝንጀሮዎችን መመልከት ያበሳጫል፤ የተረገሙ፣ ጫማ ማድረጋቸው አሁን ድረስ ምቾት አልሰጣቸውም" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ሲስቁ ይሰማል።

መገደል፣ መደፈር፣ መዘረፍ ማብቂያ የሌለው የኢትዮጵያውያን የስደት ጉዞ

ይህን ምስጢራዊ የድምጽ ቅጂ ይፋ ያወጡት በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑትና የፕሬዝዳንት ኒክሰንን የድምጽ ቅጂዎች ያሉበትን ቤተ መዘክርን ይመሩ የነበሩት ቲም ናፍታሊ ናቸው።

እነዚህ የድምጽ ቅጂዎች በብሔራዊው ቤተ መዘክር ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ለሕዝብ ይፋ ሲደረግ ፕሬዝዳንት ሬጋን በሕይወት ስለነበሩ ዘረኛ የሆነው አገላለጽ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር ሲሉ ፕሮፌሰሯ በጽሁፋቸው ገልጸዋል።

ሮናልድ ሬጋን በ2004 (እአአ) ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ሙሉው የቀድሞ ፕሬዝዳንት የድምጽ ቅጂዎች ይፋ እንዲሆኑ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ቀርቦ ከሁለት ሳምንታት በፊት እንደተፈቀደ ተገልጿል።

ናፍታሊ እንዳሉት ሬጋን ለፕሬዝዳንት ኒክሰን የደወሉት አሜሪካ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንድትወጣ ግፊት ለማድረግ ነበር፤ ነገር ግን የስልክ ውይይቱ ቀዳሚ ጉዳይ ሬጋን በአፍሪካዊያኑ የሚያቀርቡት ቅሬታ ሆነ ይላሉ።

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

ፕሬዝዳንት ኒክሰን ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከሬጋን ጋር ስላደረጉት ውይይት ሲናገሩ "እነዚህ ሰው በላዎችን ማታ በቴሌቪዥን ላይ አይቶ 'የፈጣሪ ያለህ፤ ጫማ እንኳን አያደርጉም ነበር፤ አሜሪካ እንዲህ አይነት ዕጣ ፈንታ እንዲገጥማት ሊያደርጉ ነው' ሌላም ሌላም" በማለት እንደተናገሩ ገልጸዋል።

ይፋ ስለተደረጉት የድምጽ ቅጂዎች ፕሮፈሰሯ ሲናገሩ፤ ፕሬዝዳንት ሬጋን በሮዴዢያና በደቡብ አፍሪካ ስለነበሩት የዘር መድልኦ ሥርዓቶች ያሳዩት ስለነበረው ወገንተኝነት የሚጠቁሙት ነገር ይኖራል ብለዋል።