መንግሥት በምን የሕግ አግባብ ኢንተርኔት ይዘጋል?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ Image copyright Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባሳለፍነው ሐሙስ ሐምሌ25 /2011 ዓ.ም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከልም አንዱ የኢንተርኔት መዘጋት ጉዳይ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩም የሰዎችን ሕይወትና ንብረት ከጥቃት ለማትረፍ አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ለሳምንት ሳይሆን እስከ ወዲያኛው ኢንተርኔት ሊዘጋ ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል። ለመሆኑ መንግሥት በምን የሕግ አግባብ ኢንተርኔት ይዘጋል?

የኢንተርኔቱን ባልቦላ ማን አጠፋው?

ጠብ አጫሪና ጥቃት አድራሽ የፌስቡክ ፖስቶችን እንዴት ሪፖርት ማድረግ ይቻላል?

የሕግ ባለሙያው አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ፤ በሰብዓዊ መብቶችም ሆነ በሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች መንግሥት የሃገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ሲል እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል ይላሉ።

ተመሳሳይ ጥያቄ የሰነዘርንላቸው የ "ግርምተ ሳይቴክ" መጽሐፍ ደራሲና በዓለማችን ላይ በፎርቹን መጽሔት ዝርዝር በዓለም ላይ በ2018 ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ 500 ድርጅቶች (Fortune500) መካከል በአንዱ የቴክኖሎጂ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ካሳ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ እንደተቀመጠና የሕዝብን ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አካል፤ በፌስቡክ የሚሰራጭ መረጃ የሚያደርሰውን ጉዳት ትኩረት ሰጥተው ማየታቸው የሚጠበቅ ነው ይላሉ።

መንግሥታት ኢንተርኔት ለምን ይዘጋሉ?

በሀገራችን ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የታየው የኢንተርኔት መዘጋት የዜጎችን መረጃ መቆጣጠሪያ መንገድ በመሆን መንግሥት ያለአግባብ እየተጠቀመበት ነው ይላሉ - የሕግ ባለሙያው አቶ ምስጋናው።

አክለውም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ኢንተርኔትን የሚያቋርጡ መንግሥታት የሚሞግታቸውን ሀሳብ በኢንተርኔት እንዳይንሸራሸር የመከልከያ መንገድ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው የሚል ትችት እንደሚሰነዘርባቸው ያነሳሉ።

የቴክ ቶክ የቴሌቪዥን መርሀ ግብር አዘጋጅና አቅራቢው አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ኢንተርኔትን ማቋረጥ በመላው ዓለም እየተለመደ መጥቷል ሲሉ ከሕግ ባለሙያው ሀሳብ ጋር ይስማማሉ።

ምክንያቱ ምንድን ነው? ለሚለውም የተደረጉ ጥናቶችን በመጥቀስ፤ መንግሥት የፖለቲካውና የመረጃ ቁጥጥሩ በእርሱ ሥር እንዲሆን ወይም የፖለቲካ ትርክቱን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለማስኬድ ሲፈልግ ነው ይላሉ።

መንግሥታት 'ኢንተርኔት የዘጋነው የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስተካከልና ለመቆጣጠር ነው' ቢሉም፤ ጥናቶች የሚያሳዩት ግን መንግሥታቱ የሚሰጡት ምክንያት ሽፋን መሆኑን ነው ይላሉ አቶ ሰለሞን።

ኢንተርኔት ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለው እአአ በ2010 በአረብ አብዮት መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን "ከዚያ በኋላ መንግሥታት በንቃት የሚከታተሉት ጉደይ ቢኖር ኢንተርኔትን ነው" ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄዱ ጥናቶችንም በመጥቀስ ከአረብ አብዮት በኋላ ከአርባ ሃገራት በላይ ከ400 ጊዜ በላይ ኢንተርኔት መዝጋታቸውን በአስረጂነት ያቀርባሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ ምስጋናው በበኩላቸው የምርጫ ወቅት እየደረሰ መሆኑንና የሲዳማ ክልል ለመሆን የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ በቅርብ መሆኑን በማስታወስ "ካለንበት የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር፤ በተቻለ መጠን ሀሳቦች በደንብ ተሠራጭተው ሌላ የሚገዳደራቸው ሀሳብ እየቀረበባቸው መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ ስልትን ብንጠቀም ነው የሚያዋጣን " ሲሉ አማራጭ ሃሳብ ያቀርባሉ።

የዓለም ገራት ራስምታት

በፌስቡክ በስፋት የሚሰራጩ ግጭትን የሚያስነሱ መልዕክቶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለምና የፌስቡክ ተቋምም ራስ ምታት እንደሆነ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።

ችግሩ አራት አይነት ነው። ቀዳሚው ከፍቶ ለማየት የሚያጓጉ ማስፈንጠሪዎችና አሰቃቂ ምስሎች ናቸው። ከታዋቂ ሰዎች ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ ወሬዎች፣ እንዲሁም ከጥላቻ፣ ከፖለቲካና ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ወሬዎች እንሚገኙበት የቴክኖሎጂ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ፅንፈኛ ፅሁፎችና ምስሎች ፌስቡክ ላይ እንደሚሰራጩ በማንሳት "እንደዚህ አይነት መረጃዎች የሀሳብ ግጭት ብቻ ሳይሆን የአካል ግጭት ውስጥም ይከታሉ" ይላሉ።

አይሸወዱ፡ እውነቱን ከሐሰት ይለዩ

«ኢትዮ-ቴሌኮምን እንከሳለን» የሕግ ባለሙያዎች

ሐሰተኛ ዜና ሌላው የዓለም ራስ ምታት መሆኑን የሚያትቱት አቶ ሰለሞን፤ በርካታ ሰዎች በቀላሉ እንዲታለሉ ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ተቀናብሮ የሚቀርብ ነው መሆኑን ያስረዳሉ።

Image copyright Solomon Kassa

የጥላቻ ንግግሮችም የፌስቡክና የመንግሥታት ራስ ምታት መሆናቸውን የሚጠቅሱት አቶ ሰለሞን፤ እነዚህ በዘር፣ በፆታ፣ በሐይማኖት ላይ የሚሰነዘሩ ናቸው ይላሉ።

በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ምህዳር ምክንያት፣ በብሔር፣ በሐይማኖትና በጾታ ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ ዜናዎች ተስፋተው እንደሚታይ የሕግ ባለሙያው አቶ ምስጋናውም ሆኑ አቶ ሰለሞን ይስማማሉ።

ኢንተርኔት መዝጋት መፍትሔ ይሆናል?

አቶ ምስጋናው እና አቶ ሰለሞን፤ ኢንተርኔትን መዝጋት የብሔር ግጭቶችትንም ሆነ መፈናቀልን አያስቆምም ይላሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ ኢንተርኔት ከማቋረጥ ይልቅ ግጭት ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ ዜናዎች በዋናነት የሚሰራጩበትን የፌስቡክ ተቋም ማነጋገር ተገቢ ነው። ይህንን ካደረጉ አገራት መካከል ጀርመንና ፊሊፒንስን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

መንግሥት፤ ከ100 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት አገር ውስጥ ግጭት ቢፈጠርና አለመረጋጋት ቢቀጥል፤ ቀውሱ ለአህጉሪቱ እንደሚተርፍ ለፌስቡክ ቢያስረዳ፤ ከፌስቡክ ጋር የጥላቻ ንግግሮችን በመቆጣጠር ረገድ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ መሥራት ይቻላል የሚል ሀሳብ ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ ግለሰቦችን አቅርቦ ከፌስቡክ ጋራ በቅርበት ቢሠራ ውጤት ሊያመጣ የሚችል የቁጥጥር እርምጃ መውሰድ ይቻላል ሲሉም ምክራቸውን ያጠናክራሉ።

የሕግ ባለሙያው በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት በአገራችን እየተደረገ ያለው የኢንተርኔት መዝጋት የዘፈቀደ ይመስላል በማለት፤ "አንዳንድ ጊዜ የሕዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች ሲከሰቱ ይዘጋል፤ አንዳንዴ ግን ፈተና ለማከናወንም ይዘጋል" ሲሉ ትዝብታቸውን ያጋራሉ።

ማን እንደሚዘጋውም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ በመጥቀስ "ማን ነው የሚዘጋው? ቴሌ ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው? ወይስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት? ሲሉ በመጠየቅ ይህንን የሚወስን በግልፅ የተቀመጠ መመሪያ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

በሞባይል ኢንተርኔት መቋረጥ የተገደቡ እንቅስቃሴዎች

ስመ ጥሩ ጋዜጠኛ ሃሰተኛ ዜና በመፈብረክ ከስራው ተባረረ

መንግሥት የአገርንና የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ሥራው ስለሆነ ባሻው ጊዜ እየተነሳ ኢንተርኔት እንዲዘጋ የምንፈቅድለት ከሆነ፤ ሕግ ሲጥስ የምንቆጣጠርበት ሥርዐት አይኖረንም በማለት የሕጉን አስፈላጊነት ያስረዳሉ።

ኢንተርኔት በመዝጋት የሚደርሱ ኪሳራዎች

አቶ ምስጋናው በቅርቡ ቴሌ በሰጠው መግለጫ ላይ በኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት የደረሰበትን ኪሳራ መግለፁን በማንሳት፤ የሚኖረውን ምጣኔ ገብታዊ ጉዳት ያሳያሉ።

በአሜሪካ ያለ አንድ ተቋም ያወጣው ጥናት እንደሚያሳየው፤ ኢንተርኔት በተዘጋ ቁጥር በአንድ አገር ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ በአማካይ 1.9 በመቶ ኪሳራ ያመጣል የሚሉት ደግሞ አቶ ሰለሞን ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ይላሉ አቶ ሰለሞን፤ ገንዘብ የሚለግሱ አገራት የመንግሥት አስተዳዳራዊ ተግባር በኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ሲጓተት ተሰላችተውና ተስፋ ቆርጠው ሀሳባቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ ሲሉ ያለውን ተፅዕኖ ያስረዳሉ። ኢንተርኔት ከሕክምና አገልግሎት ጋር ተያያዥ መሆኑንም በማንሳት መዘጋቱን እንደቀላል ማየት እንደሌለብን ያሳስባሉ።

ኢንተርኔት ሲዘጋ፤ "ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነባችውን ምስል በማጠልሸት ጉዳት ማድረሱ አይቀርም" የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ግጭትን ለማስቆም በሚል ኢንተርኔት ሲዘጋ፤ ግጭት ፈጣሪዎቹ ኢንተርኔት ቢዘጋ ሌላ መንገድ ያጣሉ ወይ? ብሎ መጠየቅ እንደሚያሻ ይገልጻሉ።

አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑን ያሰምሩበታል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ