ኡጋንዳዊቷ ፕሮፌሰር ፍርድ ቤቱ የወሰነባትን እስር በመቃወም እርቃኗን ወጣች

ስቴላ ኒያንዚ Image copyright Reuters

ኡጋንዳዊቷ ምሁር ፕሮፌሰር ስቴላ ንያንዚ የአገሪቷን ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን አፀያፊ ቃል በመሰንዘር አዋርደሻል በሚል የአስራ ስምንት ወራት እስር ተፈረዳባት።

የኢንተርኔት ትንኮሳ በሚል ወንጀል ፍርድ ቤቱ እስር መወሰኑን ተከትሎ ፍርዱን የኡጋንዳ ሐሳብብ በነፃነት የመግለፅ መብትን የሸረሸረ በሚል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተቹት ነው።

አርብ እለት የተካሄደውን የፍርድ ሂደት በቪዲዮ የታደመችው ፕሮፌሰር ስቴላ ውሳኔውን ስትሰማ ጡቶቿን በማውጣት ተቃውሞዋን ገልፃለች።

"ማንም መብታችንን ሊሰጠን ስለማይችል፤ ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው"

ሻደይ፦ለሴቶች፣ በሴቶች ፌስቲቫል

"አፀያፊ ኮሚዩኒኬሽን" በሚልም ክስ ቀርቦባት የነበረ ሲሆን እሱ ግን ውድቅ የተደረገው ከዚህ ውሳኔ በአንድ ቀን ቀደም ብሎ ሐሙስ እለት።

ይህ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ በስሜት የተሞላ ንግግር ያደረገችው ፕሮፌሰሯ በውሳኔው ማዘኗን ስትገልፅ ደጋፊዎቿም ድጋፋቸውን ገልፀዋል።

"ሙሴቪኒን የማበሳጨት እቅድ አለኝ፤ አምባገንነቱ አድክሞናል፣ በቃን" ብላለች።

የመናገር ነፃነትን በተመለከተ ኡጋንዳ ብዙም የማያወላዳ አካሄድ እንዳላት ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ የገለፀ ሲሆን ሙሴቪኒንም ምንም አይነት ትችትን አይቀበሉም ብሏቸዋል።

በዚህ አመት መጀመሪያ ህገወጥ የመንግሥት መድኃኒት ሽያጭ ላይ የምርመራ ጋዜጠኝነት እየሰሩ የነበሩ የቢቢሲ ጋዜጠኞችም መታሰራቸው የሚታወስ ነው።

የ44 አመቷ ስቴላ በምርምሩ ዘርፍ የላቀች ስትሆን በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ አንቱታን ከተቸራቸው ዩኒቨርስቲዎች አንዱ በሆነው ማኬሬሬ ዩኒቨርስቲም ታስተምር ነበር።

ፌስቡክ ላይ በፀረ መንግሥት ፅሁፎቿ የምትታወቀው ፕሮፌሰሯ፤ ፅሁፎቿም የግጥምን መልክ የያዙ ሲሆን "በስድብ" የተሞሉ ናቸው የሚሉም አስተያቶች ይሰማሉ።

"በዚህ ፍርድ ቤት እንደ ተጠርጣሪና እስረኛ መቅረቤ የሰፈረውን አምባገነንነት ማሳያ ነው። ስርአቱ ምንያህል አምባገነን እንደሆነ አጋልጫለሁ" በማለት ከፍርድ ውሳኔው በኋላ ፌስቡክ ገጿ ላይ የፃፈች ሲሆን አክላም "አምባገነኖችን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ታዛቢ ብቻ መሆን አልፈልግም" ብላለች።

በኢንተርኔት ትንኮሳ የሚለው ክስ የቀረበባት ባለፈው አመት ፌስቡክ ገጿ ላይ የ74አመቱን አዛውንት ፕሬዚዳንት "ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ ምነው በፈሳሹ ተቃጥሎ ቢሆን" የሚል ነገር መፃፏን ተከትሎ ነው።

ኢንጅነር አይሻ መሃመድ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

አምነስቲን ጨምሮ ብዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የፍርዱ ውሳኔ ተቀልብሶ ለሰባት ወራት እስር የቆየችው ስቴላ ነፃ እንድትወጣ ጠይቀዋል።

"የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው። የኡጋንዳ መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ የማስከበር ግዴታውን አልተወጣም፤ ይህም የሚያሳየው ምንያህል መንግሥት ለትችቶች ቦታ እንደሌለው ነው" በማለት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ጆአን ንያንዩኪ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደምም ፕሬዚዳንቱን "ጥንድ ቂጥ" በማለት በፌስቡክ ገጿ ላይ ፅፋ ለእስር ተዳርጋ የነበረ ሲሆን የፍርድ ሂደቱም እስካሁን አላለቀም።