ሶማሌ ክልል፡ የ'ጄል' ኦጋዴን የሰቆቃ ታሪኮች

የጅግጅጋ ከተማ ማረሚያ ቤት (ጄይል ኦጋዴን)

'ጄል' ኦጋዴን ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ነው የሚገኘው። ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ሰፊ ቦታን የያዘው የቀድሞ እስር ቤት ከብሎኬት በተገነባ ረዥም እና አናቱ ላይ አደገኛ ሽቦ ባለው አጥር ተከልሏል።

አሁንም ድረስ መግቢያው በር ላይ "የጅግጅጋ ከተማ ማረሚያ ቤት" ተብሎ ይጻፍበት እንጂ ይፈጸምበት በነበረው ሰቆቃ ስሙ የገነነው እስር ቤት "ጄል ኦጋዴን" በሚል ስያሜው ነው የሚታወቀው። የቀድሞ አስተዳደር እስር ቤቱ "ጄል ኦጋዴን" ተብሎ እንዳይጠራ ብዙ ጥረቶችን ስለማድረጉ ሰምተናል።

የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት በሽር አህመድ፤ ጄል ኦጋዴን ተለይቶ ይታወቅ እንጂ ስቃይ ይፈጸምባቸው የነበሩ ሌሎች ስፍራዎች እንደነበሩ ነግረውናል።

ወደ ውስጥ ተዘልቆ ሲገባ፤ በሰፊው ግቢ ውስጥ በርካታ በቅርብ ርቀት ከብሎኬት የተገነቡ ቤቶች ይታያሉ። በግቢ ውስጥ ሌላ ግቢ አለ። እንደገና በሌላኛው ግቢ ውስጥ ሌላ ግቢ ይገኛል።

አቶ አብዲ ስለተናገሩት ጉዳይ እንደማያውቅ ኢህአዴግ ገለፀ

"ከሞቱት አንለይም" የሶማሌ ክልል እስረኞች

ከዚህ ቀደም በጄል ኦጋዴን ታስረው የነበሩ ሰዎች ሲናገሩ፤ እነዚህ የተለያዩ ግቢዎች ታሳሪዎች እንደየ ደረጃቸው ስቃይን የሚቀበሉባቸው ስፍራዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።

እስር ቤቶቹ በቁጥር ነው የሚለዩት። 7ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ . . . እየተባሉ። ከእነዚህ መካከል 8ኛ ተብሎ የሚጠረው እስር ቤት ጨለማ ክፍሎች የሚገኙበት ሲሆን፤ በሽብር ወንጀል ወይም የኦብነግ አባል ወይም ድጋፍ ሰጪ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች የሚሰቃዩበት ቤት ነው።

8ኛ ተብሎ የሚጠራው ቤት ወደ በአግድም ረዘም ያለ ሲሆን፤ አራት በሮች አሉት። በእያንዳንዱ በር ዘልቀው ወደ ውስጥ ሲገባ አስር ክፍሎች ይገኛሉ።

ክፍሎቹ ሙሉ በሙሉ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጡ ናቸው። የእያንዳንዱ ክፍል ስፋት ከ10 ካሬ የሚበልጥ አይደለም። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሰቃይ ገፈትን ከቀመሱት መካከል አንዱ አሊ ሃሰን ነው።

አጭር የምስል መግለጫ አሊ ሃሰን

አሊ ሃሰን

አሊ ጄል ኦጋዴን ውስጥ ከመታሰሩ በፊት፤ የእስር ቤቱ የጥበቃ ክፍል አባል በመሆን ለ17 ዓመታት ሰርቷል። "ለሊት የጥበቃ ሥራ ላይ ሳለሁ፤ አለቃዬ 'ና እስረኞቹን ቀጥቅጥ አለኝ' እኔ አልቀጠቅጥም ብዬ ተመለስኩ። ሌላ ጊዜም ቀጥቅጥ ሲለኝ እምቢ አልኩት። ከዚያ ኮሚሽነሩ ሲሰማ 'አንተ ከኦብነግ ጋር ግንኙነት አለህ' አለኝ እና ታሰርኩ" በማለት ከእስር ቤቱ ጠባቂነት እንዴት እስረኛ እንደሆነ ይናገራል።

አሊ ለ20 ወራት 8ኛ ቤት በሚባለው እስር ቤት ውስጥ ጨለማ ክፍል ውስጥ መታሰሩን፣ ጉድጓድ ውስጥ ከእባብ ጋር ብዙ ጊዜ ማደሩን፣ ድበደባ እና በርካታ ስቃይ እንደደረሰበት ይናገራል።

"30 ሆነን እዚህ ክፍል ውስጥ እንታሰር ነበር። ክፍሉ ጠባብ ስለሆነ እንደ ውሻ ተደራርበን ነበር የምንተኛው። ተኝተን እንዳናድር አንዳንዴ ክፍሉን በውሃ ይሞሉታል" ይላል አሊ ሃሰን።

የሶማሊያ ባለስልጣናት ከአልሸባብ ጋር በተያያዘ የጎሳ መሪዎችን አስጠነቀቁ

የእስር ቤቶቹ በሮች ከላሜራ የተሰሩ ሲሆን በወለሉ እና በበሩ መካከል ክፍታት እንዳይኖር በሲሚንቶ ተደፍኗል። አሊ እንደሚለው ከሆነ ይህ የሚደረግበት ምክንያት አየር እና ብርሃን ወደ ውስጥ እንዳይገባ እንዲሁም ወደ ክፍሉ በላስቲክ ቱቦ እንዲፈስ የሚደረገው ውሃ ከክፍሉ እንዳይወጣ ለማድረግ ነው።

"ክፍሉ ውሃ ብቻ ይሆናል። ውሃ ላይ እንዴት ይተኛል?" በማለት የሚጠይቀው አሊ፤ "ውሃ ላይ መተኛት ስለማንችል ግንባራችንን ግድግዳው ላይ በመለጠፍ ተደግፈን ነው የምናድረው" ይላል።

አሊ ደርሶብኛል የሚለው ስቃይ ይህ ብቻ አይደለም። "ኑ ቤቴን ላሳያችሁ" ብሎ ከፊት ሆኖ እየመራን ወደ ሌላኛው ግቢ ይዞን ሄደ።

አሊ "ቤቴ" ብሎ የጠራው ለሽንት ቤት ፍሳሽ ማጠራቀሚያነት ታስቦ የተሰራን ጉድጓድ ነው። አሊ በዚህ ጉድጓድ ውስጥ ከእባብ ጋር አብሮ እንደታሰረ ይናገራል። "እዚህ ውስጥ ያስገቡንና ይዘጉብናል። ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ ስወጣ ደግሞ ምንም አይታየኝም" በማለት ይናገራል።

አሊ በዚህ ጉድጓድ ውስጥ በስም ከሚጠቅሰው ጋዜጠኛ ጋር መታሰሩን ያስረዳል።

ይህ ብቻም አይደለም። በጄይል ኦጋዴን ግቢ ውሰጥ የውሻ ቤት የሚያክሉ ሁለት በሽቦ የተሰሩ ቤቶች አሉ። በአንዷ ውስጥ አነር፤ በሌላኛው ቤት ውስጥ ደግሞ ጅብ ይዘው እንደነበር የጄይል ኦጋዴን ጥበቆች ነግረውናል።

በእነዚህ የውሻ ቤት በሚያክሉ ቤቶች ውስጥ ሰዎች ከጅብ እና ከአነር ጋር ይታሰሩ እንደነበር አሊ ነግሮናል። ምንም እንኳ አሊ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ባይታሰርም፤ የእስር ቤቱ ጥበቃ ሳለ ሰዎች ከአውሬዎቹ ጋር ሲታሰሩ ማየቱን ነግሮናል።

"ጅቡም ሰውዬውም ተፈራርተው ጥቅልል ብለው ጥግ ጥግ ይዘው ይቀመጣሉ" ሲል አሊ ያስታውሳል።

አክሎም "ነብሩም (አነር ነው) ይፈራል። ግን አንዳንዴ በኃይል በጥፍሩ ይቧጭራቸዋል።"

መርማሪዎቹ ይህን ሁሉ ስቃይ በታሳሪዎች ላይ የሚያደርሱት መረጃ ለማወጣጣት እንደሆነ አሊ ይናገራል። "ተናገር ይሉኛል። እኔ ግን ምንም አላውቅም። በጣም ስሰቃይ ዝም ብዬ የሰዎችን ስም እጠራለሁ። ከዚያ ሰዎቹ ተይዘው ሲመጡ ደግሞ ምንም የለም" ይላል አሊ።

አጭር የምስል መግለጫ መሪየም አብዱል

መሪየም አብዱል

ሌላዋ የዚህ ገፈት ቀማሽ የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ መሪየም አብዱል ናቸው። ወ/ሮ መሪየም "ኦብነግ ነሽ ተብዬ በጄይል ኦጋዴን እና በቃሊቲ በጠቅላለው 10 ዓመት ከ8 ወር ታስሪያለሁ" ይላሉ።

ወ/ሮ መሪየም በጄይል ኦጋዴን የደረሰባቸወን ስቃይ ሲያስቡ እምባ ይቀድማቸዋል።

"ቀን እና ማታ ደብድበውኝ አሁን በዳይፐር ነው ያለሁት" ይላሉ። ወ/ሮ መሪየም በደረሰባቸው ድበዳባ እና ህክምና ማጣት ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ሽንታውን መቆጣጠር ስለማይችሉ ሁል ጊዜም ዳይፐር ለመጠቀም እንደሚገደዱ ይናገራሉ።

ወ/ሮ መሪየም በእርሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ታሳሪዎች ላይም ከፍተኛ የሆነ በደል ይፈጸም እንደነበር ይመሰክራሉ። "ከአንድ የእሰረኛ ክፍል ወደ ሌላኛው ለመውሰድ አንድ እጅ እና አንድ እግርን በካቴና ያስሩ ነበር። እሰቲ አስቡት አንድ እጅ እና አንድ እግር በካቴና ታስሮ መራምድ እንዴት ይቻላል?"

በሴት እስረኞች ላይም ይፈጸሙ የነበሩ የጾታ ትንኮሳዎች እጅግ አስከፊ እንደነበሩ ይናገራሉ። "ለሊት ላይ እየመጡ ቆንጆ ናቸው የሚሏቸውንና ትንሽ ዕድሜ ያላቸውን ብቻ እየመረጡ 'ነይ ለኮሚሽነር ሻይ አፍይ' ይላሉ። ለምን ሌሎቹን አሮጊት አይወስዱም?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በጄይል ኦጋዴን ህጻናት ልጆች ከእናቶቻቸው ጋር ይታሰሩ እንደነበር፤ ለአንድ እስረኛ ከበቆሎ ዱቄት የሚሰራ አንድ ቂጣ እና አንድ ብርጭቆ ሻይ ብቻ በቀን እንደሚሰጥም ያስታውሳሉ።

መንግሥት ልዩ ፖሊስን እንዲበትን አምነስቲ ጠየቀ

"የሚሰጠው አንድ ቂጣ እና አንድ ብርጭቆ ሻይ ነው። እሱን እናት ትብላ ወይስ ልጅ ይብላ?" የሚሉት ወ/ሮ መሪያም ከእርሳቸው ጋር በእስር ላይ የነበሩ እናቶች እነርሱ ለቀናት ምንም ሳይመገቡ የሚሰጣቸውን ሻይ እና ቂጣ ልጆቻቸውን ይመግቡ እንደነበር ይናገራሉ።

መርማሪዎች ለሚጠይቁት ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ለማግኘት ሲሉ በባልዲ ከሽንት ቤት የሰገራ እና የሽንት ቅልቅል እየተቀዳ በአናታቸው ላይ ያፈሱባቸው እንደነበረ እንዲሁም አስረው ለሰዓታት ፀሐይ ላይ እንዲቆዩ ይደረግ እንደነበርም ወ/ሮ መሪየም እየተንገሸገሹ ነግረውናል።

አሁንም ድረስ በባልዲ ተቀድቶ እና ደርቆ የሚገኝ የሽንት ቤት ፍሳሽ በቦታው ላይ ይገኛል።

የቤተሰብ ሰቆቃ

የጄል ኦጋዴን ሰቆቃ ለታሳሪው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብም ይተርፋል። በሰቆቃ በሚታወቀው በዚህ እስር ቤት የሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት ይታወቃሉ። ወዳጅ ዘመዱ በጄል ኦጋዴን የሚገኘበት ሰው ለደቂቃ እረፍት እንደሌለው አይሻ አህመድ ምስክር ናት።

የአይሻ አህመድ ባለቤት የመንግሥት ሰራተኛ ነበር። አይሻ በማታውቀው ምክንያት ባሏ ከሥራ ቦታው ተይዞ በጄይል ኦጋዴን ታሰረ።

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው አይሻ፤ ባለቤቷን ማየት ባትችልም እሱን ብላ በየቀኑ ወደ እስር ቤቱ ምግብ እየቋጠረች ትሄድ ነበር።

ሃሰን ፋራህ ባለፉት አስር ዓመታት በጄይል ኦጋዴን እና ጎዴ በሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ በጥበቃነት አግልግሏል። እርሱ እንደሚለው በጄይል ኦጋዴን ቤተሰብ ታሳሪዎችን እንዲጠይቁ አይፈቀድላቸውም።

ልዩ ፖሊስን ማን መሰረተው?

አይሻም ባለቤቷን አንድም ቀን በአይኗ ባታየውም ለወራት በየቀኑ ምግብ አመላልሳለች። ይሁን እንጂ ባለቤቷ የሞተው ገና እስር ቤት እንደገባ በቀናት ልዩነት ውስጥ ነበር።

ከጄል ኦጋዴን የተለቀቀ እስረኛ ነበር ባሏ እንደሞተ ለአይሻ ያረዳት። ባሏ በምን ምክንያት እንደሞተ፣ መቼ እንደሞተና አስእከሬኑ የት እንዳለ እንኳን እንደማታውቅ ትናገራለች።

የእስር ቤቱ ጠባቂ የነበረው ሃሰን ፋራህ "እስረኛ እዚህ ታሞ ከሞተ፤ ታሟል ተብሎ አስክሬኑ ከግቢ ውጪ ወዳለ ህክምና ቦታ ይላካል፤ ከዚያ እዚያው ይቀበራል። ለቤተሰብ ግን አይነገርም። ከዚህ ተፈተው የሚወጡ ሰዎች ናቸው ለቤተሰብ ሄደው እከሌ ሞቷል ብለው የሚናገሩት" ይላል።

ቤተሰብ ፍለጋ ምንም አማራጭ እንደሌለው የሚናገረው ሃሰን፤ "በተሰብ ሰው ጠፋብኝ ብሎ ቢመጣ ማን ያስገባዋል?" ሲል ይጠይቃል። ሃሰን እንደሚለው ከሆነ በእስረኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመቃወሙ እርሱም ለእስር ተዳርጎ ነበር።

አጭር የምስል መግለጫ ሐሰን ፋራህ

ፍትህ

የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር በሽር አህመድ በጄል ኦጋዴን እና በሌሎች ይፋዊ ባልሆኑ እስር ቤቶች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ መፈጸሙን ይናገራሉ።

"እስር ቤቱ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ነበር። በእንድ ወቅት ከ11 እስከ 15ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ታስረውበታል ይባል ነበር" የሚሉት ከሚሽነሩ፤ በእስር ቤቱ በርካቶች መሞታቸውን ጠቅሰው ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ የማጣራት ሥራዎች መሰራት አለበት ይላሉ።

ኮሚሽነሩ የእስር ቤቱ ኃላፊ ከነበሩት መካከል ሦስቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ያልተያዙ ሰዎች መኖራቸውንና እነሱንም ፍትህ ፊት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የወ/ሮ መዓዛ ንግግር ሌሎችንም [ክልሎች] የተመለከተ ነበር" የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በእስር ቤት ውስጥ የአካል እና አእምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመደገፍ የክልሉ መንግሥት የሚወስደው ኃላፊነት ምንድነው ፤ "ግማሽ ያክሉ የሶማሌ ህዝብ እስር ቤት ነበር። ለሁሉም ድጋፍ ማድረግ ይከብዳል" የተባሉት ኮሚሽነሩ፤ ነገር ግን የጉዳት መጠናቸው ከፍተኛ የሆነ ሰዎች ወጪ ሃገር ድረስ ሄደው እንዲታከሙ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጄል ኦጋዴን የወደፊት እጣ

ጄል ኦጋዴን ከተዘጋ ወራቶች ተቆጥረዋል። የእስር ቤቱ የወደፊት እጣውን በተመለከተ ኮሚሽነሩ "የተፈጸመውን ነገር ሁል ጊዜም ማስታወስ የሚገባን በመሆኑ ሙዚየም ለማድረግ አስበናል።"

አክለውም በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል አንድም በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት የታሰረ ሰው አለመኖሩን በልበ ሙሉነት የማረሚያ ቤቶቹ አስተዳዳሪ ይናገራሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ