የዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ የዘነበ ወላና የሕይወት እምሻው ምርጥ መጻሕፍ የትኞቹ ናቸው?

ቤተ መፅሐፍት Image copyright CANDIDA NG

ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር የዓለም የመጽሐፍ ሳምንት ተከብሯል። ዛሬ ደግሞ ኦፊሴሊያዊ ባይሆንም የመጻሕፍት ወዳጆች (አፍቃሪያን) ቀን ይከበራል። ይህ ቀን ለመጽሐፍ ቀበኞችና ወዳጆች ክብር የሚሰጥበትና የሚደነቁበት ነው።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት መጽሐፍ ማንበብ ለተዝናኖት ብቻ ሳይሆን ጤንነትን ለመጠበቅም ጠቀሜታዎች አሉት። ማንበብ ጭንቀትን ለመቀነስ፣ አዕምሮን ለማስላት፣ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ፍቱን መድኃኒትም ነው ይላሉ አጥኚዎች።

ማንበብ ስፓ ከመግባት ይሻላል?

ወመዘክር፡ ከንጉሡ ዘመን እስከዛሬ

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የሚያነቡ ሰዎች ከማያነቡት በተሻለ የሌሎችን ስሜት የመረዳት ብቃታቸውም ከፍተኛ ነው።

ታዲያ ይህ ቀን በመጻሕፍት አፍቃሪ ዘንድ የመጽሐፍ ስጦታ በመለዋወጥ፣ በመገባበዝ፣ በመደናነቅ ይከበራል። የመጻሕፍት መደርደሪያዎችን በማጽዳት እና የመጻሕፍትን አደራደር በቅጡ በማድረግ ለመጽሐፍ ያላቸውንም ፍቅርም ይገልጹበታል።

ከዚህም ባሻገር ቤተ መጻሕፍትን በመጎብኘት፤ የቤተ መጻሕፍት መግቢያ ካርድ የሌላቸው በመመዝገብ፣ የንባብ ክለቦችን በመቀላቀልም ሲያከብሩ ይስተዋላል። በዚህ ቀን ሕፃናትና ወጣቶች መጽሐፍ እንዲያነቡም ይበረታቱበታል።

የእርስዎ ምርጡ መጽሐፍ የትኛው ነው?

ከወራት በፊት የዓለም የመጽሐፍ ቀንን አስመልክቶ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመጽሐፍ ወዳጆች ለእነርሱ ምርጥ የሚሏቸውን መጽሐፍ ነግረውናል። ካነበቧቸው መጻሕፍት መካከል አንድ መምረጥ ጭንቅ ቢሆንባቸውም ይህንን ጋብዘውናል።

'እኔ የምለምነው መጽሐፍና ቆሎ ነው"

ይህን ያለችው ታዋቂዋና አንጋፋዋ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ናት። ዓለምፀሐይ ከልጅነቷ ጀምሮ በኢትዮጵያ የአማርኛ መጻሕፍት ውስጥ ታትሞ የወጣ እና እርሷ ያላነበበችው መጽሐፍ ስታገኝ ትበሳጭ እንደነበር ትናገራለች፤ ይህን ያህል ነው ለንባብ ያላት ፍቅር።

ታዲያ ለእርሷ በልብወለድ አጻጻፍ ስልት የደራሲ በዓሉ ግርማ አድናቂ ስትሆን በጋዜጣዊ የድርሰት አጻጻፍ ደግሞ ብርሃኑ ዘሪሁንን ታደንቃለች።

በግጥም ዘርፍ የሎሬት ፀጋየ ገ/መድህንን 'እሳት ወይ አበባ' ለእሷ ወደር የለውም። "

ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ከራስጌዬ የማልነጥለው መጽሐፍ ነው" ትላለች። እንዲህ እንዲህ እያለች ትዘረዝራለች። እኛ ግን አንድ ብቻ እንድትመርጥ እድል ሰጠናት። [አንዱን ካንዱ ማወዳደር ጭንቅ ነበር ለእሷ።]

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

መጻሕፍት ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው ለመምረጥ ብትቸገርም ከአማርኛ መጻሕፍት ውስጥ ፍቅር እስከ መቃብርን ትጠቅሳለች።

"የደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁን ድርሰት 'ፍቅር እስከ መቃብር'ን አንብቦ የኢትዮጵያን ታሪክ አለማወቅ አይቻልም" ትላለች። ምክንያቷ፤ የኢትዮጵያን የፍቅር፣ አርበኝነትን፣ የባላባት ሥርዓትን፣ ጀግንነትን፣ የታሪክና ባህልን የሚየሳይ በመሆኑ ለእርሷ ምርጡ መጽሐፍ ነው።

ዓለምፀሐይ ፍቅር እስከ መቃብርን የመጀመሪያ ዕትሙ እንደወጣ [በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1958 ዓ.ም] እንዳነበበችው ትናገራለች። ከዚያ በኋላ ግን ሦስት አራቴ በተደጋጋሚ ያነበበችው መጽሐፍ ነው - ፍቅር እስከ መቃብር

መጽሐፍ ማንበብ ከመውደዷ የተነሳ፤ በስደት አሜሪካ አገር ሆና እንኳን ከሃገር ቤት እንዲላክላት የምትጠይቀው መጽሐፍና ቆሎ ነው ትላለች።

"የመጀመሪያውን ድራማ አንተ፤ ሁለተኛውን እኔ እፅፈዋለሁ" ኤርሚያስ አመልጋ

ዕድሜ ጠገቧ የጥድ መፃሕፍት ቤት መደብር ትውስታ

ዓለምፀሐይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር እና በራስ ቲያትር፤ የቬነሱ ነጋዴ፣ ሐምሌት፣ ሮሜዮና ዡልየት፣ ማክቤዝ፣ 12ቱ እብዶች በከተማ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ ዋናው ተቆጣጣጣሪ እና ሌሎችም በርካታ የመድረክ ተውኔቶች ላይ በመሪ ተዋናይነት ተውናለች።

ስግብግብ ምላሴ፣ የኑዛዜው መዘዝ፣ ጤና ይስጥልኝ ዶክተር፣ ያልተከፈለ ዕዳ በተሰኙ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በመሪ ተዋናይነት ተጫውታለች።

በተውኔት እና በፊልም ፀሐፊነትና አዘጋጅነት ደግሞ አማቾቼ፣ ደማችን፣ የሞኝ ፍቅር፣ ህልመኞቹ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ይጠቀሳሉ።

አምስት የግጥም መጻሕፍትን ለንባብ አብቅታለች። ከ400 በላይ የዘፈን ግጥሞቿ ቁጥራቸው ከ48 በላይ በሚሆኑ በአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን መዜማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

"ከ10 ወዳጆችሽ አንዱ አንብቤዋለሁ ካለ እድለኛ ነሽ"

አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል በባሕር ላይ ያሳለፈው ባህረተኛና ደራሲ ዘነበ ወላም የራሱ የመጽሐፍ ግብዣ አለው።

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ማስታወሻ፣ መልህቅ፣ ልጅነት፣ ሕይወት በባህር ውስጥ እና "21 ዓመታት ፈጅቶብኛል" ያለውን የምድራችን ጀግና (Champion of the Earth) በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያጠነጥን እና በዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ ላይ ትኩረት አድርጎ የተጻፈ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ አብቅቷል።

ለንባብ ባህል አብዝቶ የሚቆረቆረው ዘነበ ይህንኑ የሚሰብክ የቴሌቪዥን ፕሮግራምም ያዘጋጃል።

"የረጅም ጊዜ የንባብ ሕይወት ካሳለፍሽ አንድ መጽሐፍ መምረጥ አስቸጋሪ ነው" የሚለው ዘነበ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የጻፉት 'መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር' የሕይወት ዘመን መጽሐፉ እንደሆነ ይናገራል።

ሌላው የተክለሃዋሪያት ተክለማሪያም ግለ ታሪክ የሆነውን መጽሐፍ "ለልጅ ልጅ መተላለፍ የሚገባው መጽሐፍ ነው" ይላል። ዘነበ በርካታ መጻሕፍትን ስም መዘርዘር ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ለእርሱ ምርጥ የሆነውን አንድ መጽሐፍ እንዲጋብዘን ጠየቅነው፤ እርሱም እንዲህ አለ።

ክረምትና ንባብ

"አንድ አማርኛ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ የሚችል ሰው፤ ላንብብ ቢልና አዋቂ ልሁን ቢል፤ ዓለም አቀፍ ዕውቀት እንዲኖረው የሚያስችሉ ሥራዎች በአማርኛ ተሠርተዋል" ሲል ይንደረደራል።

ነገር ግን ለዘነበ ወላ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝን 'መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደርን' የሚያህልበት ግን የለም፤ ሁልጊዜም የእርሱን ያስቀድማል።

'መንግሥትና የሕዝበ አስተዳደር' ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ፣ በኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር ላይ እንዲሁም በሌሎች ጠንካራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መጻፉ ደራሲው በዚያ ዘመን ምን ያህል ሰፊና ጥልቅ ሕሊና እንዳለው ስለሚያሳየው መጽሐፉን ይመርጠዋል።

ገብረሕይወት ሕይወቱ ሲያልፍ "ገብረሕይወት አረፈ፤ እንደ እሱ ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው፤ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ 10 ሰው እንኳን አልነበራትም" ሲሉ ልዑል ራስ እምሩ መጻፋቸውን ዘነበ ያወሳል።

"መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር በትምህርት ሥርዓት ውስጥ መካተት ያለበት ሐሳብን የያዘ ነው" የሚለው ዘነበ ወደፊት ጠንክሮ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ እንደሆነም ነግሮናል። መጽሐፉንም እንድታነቡት ጋብዟል።

"መምረጥ ከባድ ቢሆንም ፤ ከልብ ወለድ አለንጋና ምስርን እመርጣለሁ"

ሕይወት እምሻው 'ነቆራና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር' በተሰኘ የፌስ ቡክ ገጿ በምትፅፋቸው ጽሑፎች ትታወቃለች።

በዚህ ገጿ የግል ምልከታዋን፣ ማህበራዊ ትዝብቷንና ልብ ወለድ ሥራዎችን ታቀርብበታለች። በርካታ ተከታዮችን ማፍራትም ችላለች። ባርቾ፣ ፍቅፋቂ እና ከሰሞኑ ደግሞ ማታ ማታ የሚሉ መጻሕፍትንም ለንባብ አብቅታለች።

እንደሌሎቹ ሁሉ ሕይወት እምሻውም መጽሐፍ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ አንደኛውን ከአንደኛው ለመምረጥ ብትቸገርም በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የሕይወት ዘመን ምርጥ ደራሲ አዳም ረታ እንደሆነ ገልጻልናለች።

ከአዳም ረታ ሥራዎች መካከልም 'አለንጋና ምስር'ን ታስቀድማለች። ምክንያቷ ደግሞ የሰውን ልጅ ኑሮ፤ በተለያየ ደረጃና ዘመን ያሉ የኢትዮጵያዊያንን ኑሮ በተለያዩ ታሪኮች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ አካቶ ስላቀረበ ነው ትላለች።

'ደራሲ ያደረገኝ ማኅበራዊ ሚዲያው ነው'

የእናንተስ ምርጡ መጽሐፍ የትኛው ነው? . . . ለምን?

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ