ቶርፖት ናያሪክጎር፡ ወባን በቀላሉ የሚለይ የፈጠራ ሥራ የሠራው ኢትዮጵያዊ

ቶርፖት Image copyright Icog Labs

ቶርፖት ናያሪክጎር ሮምዶር ተወልዶ ያደገው ጋምቤላ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አሶሳም አዲስ አበባም እያለ የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኩየራ አድቬንቲስት ሚሽን ተምሮ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ጋምቤላ መሰናዶ ትምህርት ቤት አጠናቋል።

ቶርፖት በአሁኑ ሰዓት በዲላ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት የኤክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው።

ቶርፖት ወንድሙን ያጣው በወባ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳል። ወንድሙ ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ በክልሉ በወባ የሚያዙና የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ቤተሰቦቹ ጋር በቆየበት ጊዜ ሁሉ ታዝቧል።

የብስክሌት ጀልባ የሠራው ወጣት

ወባ አጥፊው ክትባት ሙከራ ላይ ሊውል ነው

ይህቺን የቀዬውን ነዋሪ ሁሉ አቅም ነስታ ከአልጋ የምታውል በሽታ እንዴት በቀላሉ ማከም አልተቻለም? በቶርፖት የልጅነት አዕምሮው ውስጥ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር።

"በክልሉ ውስጥ ወንድሜ በሞተበት ጊዜ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወባን ለማጥፋት አጎበር ያከፋፍሉ ነበር" ሲል የሚያስታውሰው ቶርፖት ጤና ጣቢያው ከቤተሰቦቹ ቤት የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ያህል እንደሚርቅ ይናገራል። በዚህም ምክንያት ሕክምናን በቶሎ ለማግኘት አዳጋች ነበር።

ወንድሙ በወባ ምክንያት ሲሞት፣ ወባን ከምድረ ገፅ ማጥፋት እንዳለበት አሰበ፤ እንዴት? ምንም እውቀቱ አልነበረውም። ብቻ ዳግመኛ ወባ ቤተሰቡ ውስጥ ገብታ አንዱን የቤተሰቡን አባል በሞት ስትነጥቅ ማሰብ አልፈለገም።

ቶርፖት በዲላ ዩኒቨርስቲ

ዩኒቨርስቲ ገብቶ ራሱን በእውቀት ሲያደረጅ፣ በቴክኖሎጂው መስክ ወባን የመከላከል ብልሀት ብልጭ አለለት። በዚህ መካከል ደግሞ ሁዋዌ ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲ ጎራ አለ።

አደገኛ የተባለ የወባ በሽታ በበርካታ ሀገራት ስጋት ፈጥሯል። በኢትዮጵያስ?

የሁዋዌ ዲላ ዩኒቨርስቲ መምጣት ለተማሪዎቹ የአንድ ወር ሥልጠና ለመስጠት ነበር። ከሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ ሥልጠናው ከወሰደ በኋላ እስቲ እውቀቱ ይመዘን ተብሎ ለፈተና ተቀመጠ።

ፈተናው ለቶርፖት ከባድ አልነበረም፤ አለፈ፤ እነርሱ ደግሞ በምላሹ አዲስ አበባ ወሰዱት። ውድድሩ በዚህ አላበቃም።

አዲስ አበባ ሄዶ ደግሞ ከሌሎች ጋር ለውድድር ተቀመጠ፤ ይህንንም በድል አጠናቀቀ።

ያኔ ወደ ቻይና መጓዝ የሚያስችለው ቲኬት ተቆረጠለት። ቻይና የሁዋዌ ዋና መናገሻ ወደ ሆነው ሼንዘን በማምራት በዚህ ግዙፍ ተቋም ውስጥ የአይሲቲን ቴክኖሎጂ ያያሉ፤ ይዳስሳሉ፤ ይጨብጣሉ።

ወደ ቻይና የሄደው ከሦስት ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደነበር የሚያስታውሰው ቶርፖት ውድድራቸው ፈጠራ ላይ ሳይሆን ኔት ወርኪንግ ላይ እንደነበር ይናገራል።

የወባ ትንኝን 99 በመቶ የሚገድል ፈንገስ ተገኘ

በዚህ የሁዋዌ ግብዣ ላይ የታደሙ በርካታ አፍሪካውያንም ነበሩ። በሁዋዌ ዋና ጽህፈት ቤት ሆኖ የ5ጂ ቴክኖሎጂን ምጥቀት እና ከተማዋ እንዴት በኔትወርክ እንደተሳሰረች ተመለከተ፤ ተደመመ።

እናም ዘወትር በልቡ ያለውን ሀሳብ 'ወባን መከላከል' እውን ለማድረግ ቆረጠ። ከቻይና ሲመለስ ስለ አይኮግ ላብስ ሰማ።

የአይኮግ ላብስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ እንደሚናገሩት፣ ድርጅታቸው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋት ይሰራሉ።

ይህ ቶርፖት የተሳተፈበት ውድድርም አይኮግ ሶልቭ አይቲ (i Cog Solve IT) የሚሰኝ ሲሆን የቶርፖትን የልጅነት ሕልም ለማሳካት መንገድ የጠረገ ነበር።

ፈጠራና ቴክኖሎጂ

Image copyright Toorpoot

ቶርፖት ወባን የማጥፋት ሕልሙን ለማሳካት ቴክኖሎጂን ቀኝ እጁ አድሮጎ ተነሳ። ይህንን የፈጠራ ሥራም 'ቶር ማላሪያ ዲቴክቲንግ ዲቫይስ' ሲል ሰየመው።

"ቴክኖሎጂው ከደም ንክኪ የራቀ ነው" ይላል ስለ ስራው ሲያስረዳ። የሕመምተኛውን እጅ ስካን [በማንሳት] በማድረግ ብቻ በወባ መያዝ አለመያዙን ማወቅ እንዲያስችል አድርጎ እንደሰራው ይናገራል።

እንዴት? ግራ ለገባው ሰው መልስ አለው።

"በወባ የተያዘ ሰው ቀይ የደም ህዋስ 'ባይ ኮንኬቭ' የሆነው የሴሉ ቅርፅ በፕላስሞዲየሙ አማካኝነት ቅርፁ ይቀየራል። በዚህ ወቅት በወባ ያልተያዘና የተያዘን ሰው ሌዘር ሴንሰር ተጠቅሞ መለየት እንዲችል ማድረግ ይቻላል" ይላል ቶርፖት።

ሶፊያ ከዐብይ አሕመድ ጋር የራት ቀጠሮ ይዛለች

ይህ የሌዘር ሴንሰር የታማሚውን የጣት ምስል በመውሰድ ቀይ የደም ህዋስን የላይት ኢንቴንሲቲ ይለካል። የተለያየ ቅርፅ ያላቸው ህዋሶች የተለያየ የብርሃን ኢንቴንሲቲ ይወስዳሉ። አንድ ሰው ወባ ካለበት ፖዘቲቭ፤ ከሌለበት ደግሞ ኔጋቲቭ ላይት ኢንቴንሲቲ ያሳያል ሲል በአጭሩ ያብራራል።

ምንም ደም መውሰድ ሳያስፈልግ በጨረር ምርመራ ብቻ ተጠቅሞ እጅን ስካን በማድረግ መመርመር የሚያስችለው ይህ መሳሪያ በስልክ ላይ ተጭኖ ይሰራል ብሏል ቶርፖት።

በስልክ የተወሰደውን ምስል ወደ መመርመሪያው በኔትወርክ ወስዶ አንድ ሰው ወባ አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን በተቀመጠው ዳታ መሰረት መለየት ያስችላል ሲል ያክላል።

ይህንን የፈጠራ ሥራ በሚሰራበት ወቅትም የሦስተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው ሮቤል ከበደ ከጎኑ በመሆን እንደደገፈው ሳይገልፅ አላለፈም።

Image copyright Icog Lab

"መሳሪያውን ለመጠቀም የተራቀቀ የቴክኖሎጂ እውቀት የግድ አያስፈልግም" የሚለው ቶርፖት ማንም ሰው በቀላሉ ወባ እንዳለበትና እንደሌለበት ማወቅ እንዲያስችል ተደርጎ መሰራቱን አስረግጦ ይናገራል።

ይህ መመርመሪያ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ ተሰርቶ አለመጠናቀቁን የሚያስረዳው ቶርፖት ከግማሽ በላይ መጠናቀቁን ያብራራል።

ይህ መሳሪያ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ሥራው ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ ወባን 70 በመቶ መለየት ይችላል ሲል የሚናገረው ቶርፖት፣ ይህም የሆነበት ምክንያትም በሀገራችን በስፋት የሚገኙት የወባ ዓይነቶች ሁለት በመሆናቸው ነው ሲል ያክላል።

የሁለቱንም ወባ መረጃዎች በሚገባ አስገብቶ መመርመሪያውን ዳግም የማሻሻል ሥራው ደግሞ እየተሰራ ነው።

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

የአይኮግ ላብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት በ2010 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ውድድር ተጠናቅቆ ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉት መለየታቸውን ይናገራሉ።

ውድድሩ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል የመጡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን፤ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ከሚገኙ እና በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰር አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

ይህ ቶርፖት እየተወዳደረበት ያለው i Cog Solve IT የሁለተኛ ዙር ተሳታፊዎች የፈጠራ ሥራ ከድርጅቱ ውጪ በሚመጡ ባለሙያዎች ተመዝኖ ለአሸናፊው በቅርቡ ሽልማት እና እውቅና እንደሚሰጠው ጨምረው አስረድተዋል።

ቶርፖት ይህን መሳሪያ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ከገባ የወንድሙን ገዳይ 'ወባ'ን እንደተበቀለ ያህል ይሰማዋል።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌሎች የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ፈጠራዎች ላይ መሰማራት፣ በጋምቤላ ክልል ያሉ ወጣቶችና ታዳጊዎችን የኮምፒውተርና አይሲቲ እውቀት ከፍ ለማድረግ ለማስተማር ሕልም ሰንቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ