የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ አወጣ

ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሐምሌ 24 /2011 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶ ያፀደቃቸውን አዋጆችን ተቃውሞ መግለጫ አወጣ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 24 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ እንዲራዘምና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታዎችን ለሚለቁ ግለሰቦች የሚከፈል ካሳን ለመወሰን የሚያስችሉ አዋጆችን ማፅደቁ ይታወሳል።

የባላደራ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ምክር ቤት ምርጫ መራዘሙ በከተሞቹ ነዋሪዎችም ሆነ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው ብለዋል።

የ'ጄል' ኦጋዴን የሰቆቃ ታሪኮች

አስራ አምስት ወጣቶችን ያጣችው ኢሮብ

አሁን ያለው መስተዳድር መሬትን በሚመለከት ያለ አድልኦ ይንቀሳቀሳል በሚለው ላይ "የፍትሀዊነት ጥያቄ አለን" የሚሉት አቶ እስክንድር የሚሻለው የሚቀጥለው ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ነገሮች ባሉበተት መቆየታቸው የተሻለ መሆኑን በመግለፅ ከተማዋም ኢንቨስትመንትና ሥራ እድል በዚህ የተነሳ ይጎዳል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

"የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርም ሆነ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የከተማዋን ሕዝብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እየተንቀሳቀሱ አይደለም" ሲሉ ትቸታቸውን የሚያቀርቡት ሊቀመንበሩ ለዚህም አንድ ዓመት ተራዝሞለት የሥልጣን ጊዜውን ስለጨረሰ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ጠይቀዋል።

የሚቋቋመው ገለልተኛ አስተዳደር የፖለቲካ ወገንተኝነት ሊኖረው አይገባም ያሉት አቶ እስክንድር እስከምርጫ ድረስ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያስኬድ ሲሉ በመግለጫቸው ላይ መጠየቃቸውን ያስረዳሉ።

በገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደሩ ውስጥ ምክር ቤታቸው እንደምክር ቤት እንደማይሳተፍ የገለፁት አቶ እስክንድር፤ ነገር ግን የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ ግለሰቦች መሳተፍ ከፈለጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

እርስዎ በግልዎ ይሳተፋሉ? ተብለው ተጠይቀው ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ለዓመታት ወንድ ልጅ ያልተወለደባት ከተማ

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት "ምክትል ከንቲባውም ሆኑ በኢህአዴግ የተሞላው የመስተዳደሩ ምክር ቤት የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን ተቀብሎ ለማስፈፀም እየተንቀሳቀሰ ነው" ሲሉ ይከስሳሉ።

ምክር ቤቱ ይህንን የብዙሃኑ የከተማዋ ነዋሪ አቋም ነው ብሎ መውሰዱን የሚተቹት አቶ እስክንድር በዚህ የተነሳ የከተማዋ ሕዝብ ተወክሏል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ከተማን ያስተዳደሩት ከኦህዴድ (ኦዴፓ) የተገኙ እንደነበሩ በማስታወስ ኢንጂነር ታከለ የልዩ ጥቅሙን ለማስከበር የተለየ ያደረጉት ነገር ምንድን ነው? ተብለው በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ እስክንድር "መሰረታዊው ጥያቄው የጊዜ ነው" ይላሉ።

ከዚህ ቀደም የነበሩት ከንቲባዎች ከተማዋን ያስተዳደሩት ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወት በነበረበት ወቅት መሆኑን በመጥቀስ "አሁን ደግሞ የኦዴፓ የበላይነት በመኖሩ ጉዳዩን ለየት ያደርገዋል" ብለዋል።

አክለውም በፊት አምባገነናዊ ሥርዓት መኖሩን ይህንን የልዩ ጥቅም ጥያቄ ማንሳት አለመቻሉን በመግለፅ አሁን በከፊልም ቢሆን ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር እያደረግን ስለሆነ ጥያቄዎቹን ለማንሳት ችለናል ሲሉ ያስረዳሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ መቃወም

አቶ እስክንድር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፋቸው ሁለቱም ውሳኔዎች የአዲስ አበባን ሕዝብ ጥቅም አለማስከበር ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸው አንድምታም ጥሩ አይደለም በማለት የምክር ቤቱን ውሳኔ የተቃወሙበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

የባላደራ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር እንደሚሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ውሳኔ ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው ሳይሆን የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ትክክል አይደሉም እያሉ መሆኑን ይገልፃሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በሙሉ የሕዝብ ድጋፍ አላቸው ማለት አይደለም የሚሉት አቶ እስክንድር ውሳኔዎቹ ላይ ጥያቄ ይነሳሉ በዚያ አግባብ ነው ጥያቄ ያነሳነው ብለዋል።

ለዓመታት የተጠፋፉት የወላይታ ሶዶዋ እናትና የኖርዝ ኬሮላይናዋ ልጃቸው

ባለ አደራ ምክር ቤቱ እንዲቋቋም የሚፈልገው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ በፊት የጣሊያን ጥምር መንግሥት ሲፈርስ የተቋቁመ አይነት መሆኑን የሚያስረዱት አቶ እስክንድር ይህ ምክር ቤት እስከቀጣዩ ምርጫ ድረስ ከተማዋን በማሻገር ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ይላሉ።

የሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በፊት ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር ለማቋቋምና ወደ ሥራ ለመግባት በቂ ጊዜ አለ የሚሉት አቶ እስክንድር ይህ ጉዳይ በፍጥነት እልባት የማያገኝ ከሆነ ወደ ችግር ያድጋል የሚል ግምገማ አለን ሲሉ የምክር ቤታቸውን ስጋት ይናገራሉ።

እነዚህን ሙያተኞች አዋቅሮ ወደ ሥራ ለማስገባት አጭር ጊዜ ብቻ ነው የሚያስፈልግው የሚሉት አቶ እስክንድር ለዚህም የጣሊያንን ተሞክሮ መውሰድ ይበቃል ባይ ናቸው።

ጣሊያን ግዙፍ ኢኮኖሚና ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት የሚገመት መሆኗን በመጥቀስ ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገለልተኛ የሙያተኞች አዋቅረው ወደ ሥራ ገብተው አሳይተዋል ስለዚህ እኛም ጋ ይህንን ማድረግ ይቻላል ይላሉ።

"የሚያስፈልገን ቅንነትና የፖለቲካ ቁርጠንነት ነው" በማለትም የሚቀጥለው ዓመት አገራዊ ምርጫ መደረጉን እርግጠኛ አለመሆናቸውን ይገልፃሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ስለቀጣዩ ምርጫ ተጠይቀው ሲመልሱ 'ቢደረግ ጥሩ ነው ያንን ታሳቢ አድርገን ነው የምንንቀሳቀው፤ ሆኖም ግን አልወሰንም የምንወስነውም ብቻችንን አይደለም' ማለታቸውንም በመጥቀስ ምርጫው የሚቀጥለው ዓመት መደረግ አለመደረጉም አይታወቅም ሲሉ ጥያቄያቸውን ሲያነሱ ይህንንም ታሳቢ ማድረጋቸውን ያስቀምጣሉ።

"የክልሎች ልዩ ኃይልን በተመለከተ ውይይት ያስፈልጋል" የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝደንት

አዲስ አበባ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለች ሄዶ ሄዶ አንድ ቦታ ላይ ችግር ያስከትላል የሚል እምነት አለን የሚሉት አቶ እስክንድር ለዚህም ሁላችንም የምንተማመንበት፣ ከሕግም፣ ከሞራልም፣ ከፖለቲካም አኳያ ቅቡልነት ሊኖረው የሚችል ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር ይቋቋም የሚሉት ለዚህ መሆኑን ያስረዳሉ።

ምክትል ከንቲባው ምንም ጥሩ ነገር አልሰሩም?

"የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የከተማዋን ሕዝብ አይወክሉም እያልን እንጂ ምንም ጥሩ ነገር እየሰሩ አይደለም አላልንም" የሚሉት አቶ እስክንድር "ከምክትል ከንቲባው ጋር በግል ተቃውሞም ጠብም የለንም የምንከራከረው በፖለቲካ አቋማቸው ላይ፣ በወከሉትና በሚያራምዱት ሀሳብ ላይ ነው" ይላሉ።

"እርሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዋናነት የምንቃወመውና የምንታገለው የሚወክሉትን ድርጅት ኢህአዴግን ነው" በማለትም የትግላቸው ግብም በሚቀጥለው ምርጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ኢህአዴግ እንዳይመረጥ ማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ።

ቴክቫህ ኢትዮጵያ፡ የፀረ ጥላቻ ንግግር የወጣቶች እንቅስቃሴ

ኢንጂነሩንም ሆነ ኢህአዴግን ስንቃወም የአብዛኛው የከተማዋን ህዝብ ፍላጎት የማይወክሉ ስለሆነ ነው በማለትም ነገ ኢንጂነሩ ይህንን አቋማቸውን ቀይረው ምክር ቤታችንን ልቀላቀል ቢሉ ያለምንም ቂም በራችን ክፍት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

አሁን ካሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአዲስ አበባን ህዝብ ጥቅም ያስከብራል የምትሉት አለ? ተብለው የተጠየቁት አቶ እስክንድር እርሱን እያጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደምክር ቤት አቋም ሲወስዱም አቋማቸውን እንደሚገልፁ ገልጠዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ