የጅግጅጋ የአንድ ዓመት ክራሞት ምን ይመስላል?

ጅግጅጋ ኪዳነምህረት

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.፤ በጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ቀን ነበር። ማንነትንና ኃይማኖትን መሠረት ያደረገው ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወትን ቀጥፏል፣ በርካቶችን አፈናቅሏል፣ ንብረትም አውድሟል።

ከአንድ ዓመት በኋላ ሐምሌ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ላይ፤ ጥቃቱን በመሸሽ ከጅግጅጋ ወጥተው የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ወደቀደመ የተረጋጋ ሕይወታቸው ተመልሰዋል።

ተቃጥለው ከነበሩት አብያት ቤተ-ክርስቲያናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰው ተገንብተዋል።

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በተሰነዘረ ጥቃት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዷ የሆነችውና በጅግጅጋ ከተማ የምትገኘው ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን በዓመቱ ዳግም ተገንብታ ለምረቃ በቅታለች።

"ጅግጅጋ ገሬ!"

ብርቱኳን ለገሰ ምንም እንኳ ጅግጅጋን ተወልዳ ባታድግባትም፤ 20 ዓመት ያህል ኖራባታለች። ሁለት ልጆቿን ወልዳ ለመሳም የበቃችው እዚሁ ጅግጅጋ ውስጥ ነው።

ብርቱኳንን ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ስናገኛት ወሬ የጀመረችው የባለፈውን ዓመት በማስታወስ ነው።

"ከአንድ ዓመት በፊት የተፈጸመብን የፖለቲካ ሴራ እንጂ የሶማሌ ሕዝብ እንዲህ አያደርግም። ከ20 ዓመታት በላይ በዚህ ከተማ ስኖር ሕዝቡን አውቀዋለሁ። እነዛ ወጣቶች በገንዘብ ተገዝተው ነበር" ትላለች።

"የወ/ሮ መዓዛ ንግግር ሌሎችንም [ክልሎች] የተመለከተ ነበር" የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ዛሬ ላይ የ3 ልጆች እናት የሆነችው ብርቱኳን፤ ሐምሌ 28 የሶማሌ ክልል ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ ጥቃቱ ሲፈጸም፤ የ7 ወር ነብሰ ጡር ነበረች። "በዕለቱ የማደርገው ጠፍቶኝ ነፍሴ ተጨንቃ ልጆቼን የምደብቅበት አጥቼ በጨርቅ ሸፍኜያቸው ነበር" በማለት ትናገራለች።

"የ7 ወር ነፍሰጡር ስለነበርኩ ቤተሰቦቼ ጋር ሄጄ ወለድኩኝ። ከዛ ልጄ የሁለት ወር ጨቅላ እያለ የጥምቀት በዓልን የማከብረው ሃገሬ ጅግጅጋ ላይ ነው ብዬ ተመለስኩ" ትላለች።

መልዓከ ሙሄ አባ ጽጌ ደስታ የጅግጅጋ ቅዱስ ሚካዔል ደብር አስተዳዳሪ ናቸው። ከአንድ ዓመት በፊት በተቃጣው ጥቃት በቅድሚያ ዒላማ ተደርጋ የነበረችው ቤተ-ክርስቲያን መሆኗን እና ከተቃጠሉት አስሩ አብያተ-ቤተክርስቲያነት ሰባቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወድመው እንደነበረ ያስታውሳሉ።

እንደ ብርቱኳን ሁሉ አባ ጽጌም በቤተ-ክርስቲያን እና በሌሎች ላይ የተቃጣው ጥቃት እንዲፈጸም የተደረገው በተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን ያምናሉ።

"ችግሩ ከተከሰተ በኋላ በቤተ-ክርስቲያን ጉዳዮች ተይዤ በ13ኛው ቀን ነበር ወደ ቤቴ የተመለስኩት። እስከዚያው ድረስ ልጆቼን ጠብቆ ያቆየልኝ ሶማሌ ነው።" ይላሉ።

የ30 ዓመቱ ወጣት ይድነቃቸው ታደለ፤ ትውልድ እና እድገቱ ጅግጅጋ ነው። የተቃጠሉ አብያተ-ክርስቲያናት አሰሪ እና አስመራቂ ኮሚቴ አባል ነው።

"የማይቻለውን ችለን አልፈናል። ያን ወቅት እናልፈዋለን ብለን አላሰብንም ነበር። ፈጣሪ የሚሳነው የለም" የሚለው ይድነቃቸው፤ "ያን ሁሉ መዓት ባሳለፍንበት ዕለት የሞት አዋጁ ተሽሮ ይህን የመሰለ ቤተ-ክርስቲያን አስገንብተን ለማስመረቅ በመብቃታችን ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው" በማለት ስሜቱን ይገልጻል።

ሙሰጠፋ ሙሐመድ ኢጋል ደግሞ የሃገር ሽማግሌና ኡለማ ናቸው።

"የክልሎች ልዩ ኃይልን በተመለከተ ውይይት ያስፈልጋል" የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝደንት

"አንድ መደብር ከመሸ ክፍት አይሆንም ነበር። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን ሁሉም እያስቆመህ መታወቂያ ይጠይቅህ ነበር። አሁን ግን እንደፈለግህ ትንቀሳቀሳለህ። እስከ አምስት ሰዓት ድረስ ሱቅ ክፍት ነው።" በማለት ከአንድ ዓመት በፊት የነበረውን የጅግጅጋ ሁኔታ ከዛሬው ጋር ያነጻጽራሉ።

"በጅግጅጋ ያሉ ብሄሮች አብረው ይነግዳሉ፣ አብረው ይጫወታሉ፣ አብረው ጫት ይቅማሉ። አሁን ሁሉም ሰላም ነው።" ይላሉ አቶ ሙሰጠፋ።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ሙሐመድ፤ "ዋናው ትኩረታችን መሰል ጥቃቶች በክልላችን ዳግም እንዳይከሰቱ ማድረግ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ምንም ዓይነት ችግር አልተከሰተም። ማንም ሰው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ መኖር ይችላል። ለዚህም የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል" ሲሉ በክልሉ የሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆችና የተለያዩ ኃይማኖት ተከታዮች ስጋት እንዳይገባቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ነዋሪውስ ምን ይላል?

"ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞን አያውቅም። ወደፊትም ቢሆን ከዛ የከፋ ነገር ይከሰታል ብዬ አልጠብቅም። . . . በጭራሽ ይሄ ዳግም ይመጣል ብዬ አላስብም። ድሮስ ቢሆን ይሄ ይመጣል ብለን ጠብቀናል?" ያለችው ብርቱኳን ለገሰ ነች።

ብርቱኳን በልበ ሙሉነት ይህን መሰል ጥቃት ወደፊት አይከሰትም እንድትል ካስቻሏት ምክንያቶች አንዱ፤ በክልሉ አስተዳደር ላይ ያላት እምነት ነው። "ያን ችግር ያመጣብን ፕሬዝደንት ሄዷል። አዲሱ ፕሬዝደንታችን ሙሰጠፌ ጥሩ አካሄድ ላይ ነው ያለው።" ትላለች።

መንግሥት በምን የሕግ አግባብ ኢንተርኔት ይዘጋል?

"ኦሮሞ እና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም" የትነበርሽ ንጉሤ

"ሁልጊዜም ቤተ-ክርስቲያን በፈተና መካከል ነው የምትኖረው። ፈተና ግን አያሸንፋትም" የሚሉት አባ ጽጌ "በአሁኑ ሰዓት ግን ለፈተና የሚያጋልጡ ትንኮሳዎች የሉብንም። ከክልሉ መንግሥት ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን" ይላሉ።

"ፕሬዝዳንቱ መንበረ ሥልጣናቸውን እንደተረከቡ ቀድመው የመጡት ወደ እኛ ነው። ጎብኝተውን አጽናንተውናል።" ሲሉ መልካም አስተዳደር ስለዘረጉም ከቤተ-ክርስቲያኗ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ይናገራሉ።

ይድነቃቸው በበኩሉ፤ "ይከሰታል የሚል እምነት የለኝም፤ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ምክንያቱም ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ነው። እድሜዬ 30 ነው። በዚህ ሁሉ እድሜዬ ውስጥ እንዲ ያለ ነገር ይከሰታል ብዬ አልጠበቅም ነበር። ግን ተከሰተ። በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙሰጠፌ ይህን ነገር እንደሚከላከሉ እምነት አለኝ" በማለት መጪውን መገመት አዳጋች እንደሚሆንበት ያስረዳል።

አቶ ሙስጠፌ ደግሞ "ሐምሌ 28 በጣም ችግር ፈጥሮ ነበር። ይህን የፈጠረው ግን ሕዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ደላላዎች ናቸው።" ይላሉ።

"የፖለቲካ ደላላዎች ናቸው ሰው የሚያጋጩት። እዚያ እየሄዱ ኦሮሞ ሶማሌን ገደለ ይላሉ። እዚህ ደግሞ ራሳቸው ገድለው ሶማሌ ኦሮሞን ገደለ ይላሉ። እኛ እኮ እውነቱን እናውቃለን" ብለዋል።

አቶ ሙሰጠፌ የሃገር ሽማግሌ እና የኃይማኖት መሪ እንደመሆናቸው ቀድሞውኑ ግጭቶች እንዳይከሰቱ የበኩላቸውን ለምን እንዳልተወጡ ሲያስረዱ

"ሁሉ ሰው ጄል ኦጋዴንን ይፈራል። ትንሽ ከተናገርክ ጄል ኦጋዴን ትገባለህ። ከዛ 30 ዓመት 40 ዓመት ትቀመጣለህ። አሁን ግን አዲስ ነገር መጣ። ጄል ኦጋዴን ተዘጋ። መናገር ይቻላል። ከአሁን በኋላ ማንም አያጣላንም።" ሲሉ ተስፋቸውን ያገልፃሉ።