የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት "ታዳጊዎችን ማብቂያ ለሌለው ለባርነት" እየዳረገ ነው ተባለ

ታዳጊ ሴት ምልምሎች Image copyright AFP

ኤርትራ ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር የሠላም ስምምነት ላይ ብትደርስም በብሔራዊ አገልግሎት ሰበብ ታዳጊዎችን ማብቂያ በሌለው ባርነት ውስጥ በማስገባት እየተከሰሰች ነው።

ሂማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ጭምር ለግዴታ ወታደራዊ ስልጠና እንዲገቡ እንደሚገደዱ ገልጿል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየውን የጦርነት ፍጥጫ ለማብቃት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሠላም ስምምነት ካደረገች አንድ ዓመት ቢቆጠርም የብሔራዊ አገልግሎቷ እንደቀጠለ መሆኑ ይነጋራል።

ኤርትራ፡ ''እናቶች ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ታስረዋል''

ኤርትራ በሳዋ ባደረገችው ወታደራዊ ትዕይንት ምን እያለች ይሆን?

በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ኤርትራዊያንም ይህ የብሔራዊ አገልግሎት ተሳታፊዎች የሚሰለጥኑበት አስፈሪው የሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲዘጋ የሚጠይቅ የመረጃ መረብ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ሪፖርቱ ጨምሮም ሁሉም የመጨረሻ ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በጥብቅ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት በሚተዳደሩበትና ለቀላል ጥፋቶች አስከፊ ቅጣት ወደሚፈጸምበት ሳዋ ወታደራዊ ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋል።

ከስልጠናው በኋላም የተወሰኑት በሠራዊቱ ውስጥ እንዲቆዩ፣ ሌሎች ደግሞ በመምህርነት ወይም በሌላ የመንግሥት ሥራ ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ይደረጋል።

መምህራንም በዝቅተኛ ክፍያ ማብቂያው ለማይታወቅ ጊዜ በሳዋ ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ እንዲሰሩ እንደሚገደዱ ተጠቅሷል።

ሂማን ራይትስ ዎች "እያስተማሩን ሳይሆን ባሪያ እያደረጉን ነው" በሚል ርዕስ በኤርትራ ስለሚካሄደው የግዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት ላይ ባወጣው ሪፖርት ምልመላው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መምህራንና ተማሪዎች ኤርትራን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ በሃገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ጥራት ላይ ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል ተጽእኖ እንዳለው አመልክቷል።

"ማብቂያ የሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ነው" ሲል በሳዋ ማሰልጠኛ ማዕከል ማስተማር የነበረበትና ባለፈው ዓመት ኤርትራን ጥሎ የተሰደደው የ25 ዓመቱ ወጣት ለሂማን ራይትስ ዋች ተናግሯል።

"መኖር የምፈልገው ልጆቼን ለማየት ብቻ ነው"

"አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው"- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

"የፊዚክስ ትምህርትን ለማስተማር ከተመለመልክ፤ እድሜ ልክህን ሙሉ የፊዚክስ መምህር ሆነህ ትቀራለህ።"

ባለፈው ሳምንት ኤርትራ የብሔራዊ አገልግሎቱ በከፍተኛ ደረጃ ሃገሪቱን እንደጠቀመ በመግለጽ የተጀመረበትን 25ኛ ዓመት ለቀናት በቆየ ደማቅ ሥነ ሥርዓት አክብራለች።

ብሔራዊ አገልግሎቱ እንዲቆም የሚጠይቁ ዘመቻዎችን የሚያካሂዱ ሰዎች ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ስለተሻሻለ ለውጥ ማካሄድ አለባት ይላሉ።

"አሁን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ችግር ተፈትቷል፤ ስለዚህ ከሃገሪቱ ወጣቶች መብትና ነጻነት በመጀመር በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የሚደረጉ ለውጦች ተከትለው መምጣት አለባቸው" ሲሉ በሂማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ የአፍሪካ ተመራማሪ በመግለጫው ላይ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።