በ10 ሰከንድ ውስጥ ለስርቆት የተጋለጡት ዘመናዊ መኪኖች

ለስርቆት የተጋለጡት መኪኖች Image copyright What Car?

አዲስ ተመርተው ገበያ ላይ ከዋሉት እጅግ ዘመናዊ ታዋቂ መኪኖች መካከል አንዳንዶቹ ካለቁልፍ የመንቀሳቀስ ሥርዓታቸው ላይ በተገኘ ደካማ ጎን ሳቢያ ለስርቆት እየተጋለጡ መሆናቸው ብዙዎችን እያሳሰበ ነው።

የመኪኖቹ አሰራር አሽከርካሪው ምንም ቁልፍ ሳያስፈልገው መኪናውን ከፍቶ ለመግባት የሚያስችል ነው።

በተሽከርካሪዎች ጉዳይ ላይ የሚያተኩር አንድ እንግሊዝ ውስጥ የሚታተም መጽሔት ካለ ቁልፍ በሚከፈቱና ሞተራቸው በሚነሳ ሰባት የተለያዩ መኪኖች ላይ ሙከራ አድርጎ ነበር።

የተለያየ ስያሜ ያላቸው የአውዲ፣ የላንድሮቨርና የሌሎች መኪኖች ዘመናዊ ስሪቶች ከባለቤቶቻቸው ውጪ መኪኖቹን ለመስረቅ ከፍቶ ለመግባትና አስነስቶ ለመሄድ አስር ሰከንዶች ብቻ ናቸው የወሰዱት።

በደቡብ አፍሪካ እስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ

ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ፡ «ስለተተከሉት ዛፎች ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ የለም»

የህዋ ጣቢያዋ ዛሬ ማታ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ ትታያለች

የተሽከርካሪ ደህንነት ባለሙያዎች ሙከራውን ያደረጉት የመኪና ሌቦች የሚጠቀሙትን ዘዴ ተግባራዊ በማድረግ ነው ሲል መጽሔቱ ዘግቧል።

ባለሙያዎቹ ባደረጉት ሙከራ መኪኖቹን ከፍቶ ለመግባትና አስነስቶ ለመውሰድ የፈጀውን ጊዜ መዝግበው የያዙ ሲሆን፤ በውጤቱም ከሚጠበቀው በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ሌቦቹ መኪኖቹን ለመስረቅ እንደሚችሉ ደርሰውበታል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የመኪና ስርቆት በኢንግላንድና ዌልስ ውስጥ ባለፉት ስምንት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከ106 ሺህ በላይ መኪኖች ተሰርቀዋል።

በዚህም ሳቢያ ባለንበት ዓመት መኪኖቻቸው የተሰረቁባቸው ሰዎች የጠየቁት የኢንሹራንስ ክፍያ መጠን በሰባት ዓመታት ውስጥ ከታየው ከፍተኛው መጠን እንደሆነም ተነግሯል።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደሚሉት በመኪኖች ስርቆት ምክንያት እየተጠየቁ ላሉት ክፍያዎች ማሻቀብ ቁልፍ አልባ ዘመናዊ መኪኖች ከፊል ምክንያቶች እንደሆኑ ያምናሉ።

ለስርቆት የተጋለጡት መኪኖች አምራች ኩባንያዎች ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገልጸው፤ ምርቶቻቸውን ለስርቆት ተጋላጭ ያደረገውን ምክንያት ከፖሊስ ጋር በመተባባር ለይተው መፍትሄ በማግኘት የተሽከርካሪዎቻቸው ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተሽከርካሪዎችን በመሸጥ የሚታወቁ ድርጅቶች ለስርቆት የተጋለጠውን ዘመናዊውን የመኪኖች ቁልፍ አልባ ሥርዓት በባለቤቶቹ ፍላጎት መሰረት እንዳይሰራ ማድረግ እንዲችሉ እንደተፈቀደ ተገልጿል።

Image copyright Getty Images

ቁልፍ አልባ መኪኖቹ እንዴት ይሰረቃሉ?

እንዲህ አይነት መኪኖችን የሚሰርቁ ሌቦች በተለምዶ ሁለት በመሆን ነው ለስርቆት የሚሰማሩት። በአብዛኛው ኢላማ የሚያደርጓቸው መኪኖች ደግሞ ከቤት ውጪ የቆሙ መኪኖችን ነው።

አንደኛው ሌባ መኪናውን ለመክፈት የሚጠቀሙበትን ዘመናዊ መሳሪያ ይዞ ከመኪናው አቅራቢያ ይቆማል፤ ሌላኛው ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ መሳሪያ ይዞ ከቤቱ አቅራቢያ ይቆማል። ከሁለቱ መሳሪያዎች የሚለቀቀው የጨረር መልዕክት የመኪናው ሥርዓት ላይ ግራ መጋባትን በመፍጠር እንዲከፈት ያደርገዋል።

ሌቦቹ መኪናውን ከሰረቁ በኋላ ጠቃሚ አካላቱን ለያይተው እንደሚወስዱ ፖሊስ ይናገራል።

ይህንን የቁልፍ አልባ መኪኖች ስርቆትን ለመከላከል መኪና አምራቾች እንቅስቃሴን የሚለይ ቴክኖሎጂን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ ጀምረዋል።

በመኪኖቹ ላይ ሙከራ ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚሉት ስርቆትን ለመከላከል ሲባል እንቅስቃሴን የሚለየው ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸውን መኪኖች ለመክፈት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።

በዚህም ቴክኖሎጂው የመኪና ስርቆትን ለመከላከል አስተማማኝ መሆኑን ደርሰውበታል። ቢሆንም ግን ይህ ዘመናዊ የመኪና ስርቆት መከላከያ ቴክኖሎጂ በገበያው ላይ በስፋት አይገኝም።