ሊቦከምከም፡ በጎርፉ ሳቢያ ቢያንስ 400 ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ ተባለ

በጎርፍ የተጥለቀለቀ ቦታ Image copyright AMMA

በፎገራ እና ሊቦከምከም ወረዳ የርብና ጉማራ ወንዞች ሞልተው በመፍሰሳቸው በአካባቢው የሚገኙ ቀበሌዎች አጥለቅልቀዋል።

በዚህም ሳቢያ በሊቦከምከም ወረዳ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በሰብል ላይ የደረሰው ውድመት በውል ባይታወቅም ጉዳት መድረሱን የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብራራው ምህረት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድም ሴት የፓርላማ አባል የሌላት ሃገር

ሰዎችን ከሲኖ ትራክ የገለበጠው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

የሁለቱ ግለሰቦችም ሕይወት ያለፈው ከአካባቢው በዋና ለመውጣት ሲሞክሩ ቀድሞ ተቆፍሮ ከነበረ ጉድጓድ ውስጥ በመግባታቸው ነው ብለዋል።

አቶ አብራራው እንደነገሩን ከሆነም በጎርፍ መጥለቅለቁ ሳቢያም ቢያንስ 400 የሚሆኑ ሰዎችም በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ይገኛሉ።

አካባቢው ሩዝ አምራች መሆኑ ያስታወሱት አቶ አብራረው፤ በሰብሉ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያክል እንደሆነ አሁን ላይ እንዳልታወቀ ኃላፊው አክለዋል።

በወረዳው የሚገኙት ጥማጋና ካብ ቀበሌዎችም በውሃ መጥለቅለቃቸውን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቁ ካጋጠመ በኋላ የክልሉ መንግሥት ወደ ሥፍራው ጀልባዎችን በመላኩ ሰዎች ጉዳት ሳያጋጥማቸው መውጣት መቻላቸውንና በአካባቢው ባለው አቅራቢያ ቀበሌ በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ እንደተጠለሉ ይናገራሉ።

"አብዛኛው ሰው ቤቱን እና ንብረቱን ጥሎ መውጣት አይፈልግም፤ ነገር ግን ፈቃደኛ የሆኑት መውጣት ችለዋል" የሚሉት ኃላፊው በመጠለያ ጣቢያው ሴቶች፣ ህፃናት እና አዛውንቶች እንደሚገኙበት ገልፀውልናል።

ቤት እና ንብረታቸውን ጥለው ከወጡት መካከል ዋና የሚችሉት አሁንም ወደ ቀያቸው እየሄዱ ቤታቸውን እንደሚያዩ ነግረውናል።

የብስክሌት ጀልባ የሠራው ወጣት

ከዚህ ቀደምም በክረምት ወራት በአካባቢው ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ እንደነበረ የሚናገሩት አቶ አብራራው፤ ከዚህ ቀደም ተፋሰሶችን በመስራትና፤ በበጋ ወቅት የተቆፈሩ ጉድጓዶችን በመድፈን ጥንቃቄዎች ይደረጉ ነበር ይላሉ።

ይሁን እንጂ የዘንድሮው የክረምት ዝናብ መጠን ከፍ በማለቱ እና ግድቦቹ በመሙላታቸው አደጋው እንዳጋጠመ አስረድተዋል። የቦታው መልከዓ ምድር አቀማመጥ ሜዳማ በመሆኑ ለእንዲህ ዓይነት መጥለቅለቅ የመጋለጡ እድል ሰፊ እንደሆነም ያስረዳሉ።

አጎራባች ወረዳ የሆነው ፎገራ ወረዳም እንዲሁ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋው አጋጥሞታል። ያነጋገርናቸው የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉነህ አበበ በዘንድሮው ክረምት ሐምሌ ወር ላይ የተረጋጋ ክረምት ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ።

ይሁን እንጂ ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ለረጅም ሰዓት የሚጥለው ኃይለኛው ዝናብ የርብ ወንዝና የጉማራ ወንዝ በመሙላታቸው የጎርፍ መጥለቅለቁ እንደተከሰተ ይናገራሉ።

በወረዳው ባሉ 6 ቀበሌዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስና የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ለማድረግ እንደተቸገሩ ያስረዳሉ።

በቤት እንስሳትና የእንስሳት ግጦሽ፣ እንዲሁም ሰብል ላይ [ በተለይ የተዘጋጁና በጎተራ የተቀመጡ ሰብሎች ላይ] ላይ መጠነኛ ጉዳት ከመድረሱ በስተቀር በፎገራ ወረዳው ቀያቸውን ለቀው የወጡና ሕይታቸው ያለፉ ሰዎች አለመኖራቸውን አክለዋል።

ከጎርፉ ጋር ተያይዞ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የውሃ ማከሚያ ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ክረምቱም ከዚህ እየከፋ ከሄደ ምን መደረግ አለበት በሚል በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ውሃውን የማፋሰሻ ቦታዎች እየሰሩ መሆናቸውንና አደጋው ቢከሰት ጊዜያዊ መጠለያ ለመስራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ