ቫኑዋቱ፡ አንድም ሴት የፓርላማ አባል የሌላት ሃገር

ያስሚን Image copyright Chris Morgan/BBC
አጭር የምስል መግለጫ ያስሚን

ቫኑዋቱ ስለምትባል ሃገር ሰምተው ያውቃሉ? ቫኑዋቱ በዜናዎች ላይ ብዙም ባትነሳም አሁን ግን አንዲትም ሴት አባል በፓርላማዋ ውስጥ ባለመኖሯ መነጋገሪያ ሆናለች።

ቫኑዋቱ በደቡባዊ ፓሲፊክ ውቅያኖስ 1300 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያሉ 80 ደሴቶችን የያዘች ሃገር ስትሆን ፓርላማዋም 52 አባላት ያሉት ሲሆን ሁሉም እንደራሴዎች ግን ወንዶች ናቸው።

ለሴቶች የተከለከለ ተራራን የወጣችው የመጀመሪያ ሴት

የፓርላማ አባሉ ሴት ባልደረባቸውን በመምታታቸው ተያዙ

በዚህም ሳቢያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ በሕግ አውጪው ምክር ቤት ሴቶች እንዲወከሉና የሴቶች እኩልነት ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት የምታደርገው ያስሚን ትናገራለች።

ለነገሩ ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ፓርላማ ያላት ቫኑዋቱ ብቻ ሳትሆን በዓለማችን ሌሎች ሁለት ሃገራትም በምክር ቤታቸው ውስጥ አንዲትም ሴት በአባልነት አትገኝም።

በአጋጣሚ በፓርላማቸው ውስጥ ሴት የምክር ቤት አባላት የሌላቸው ሃገራት ቫኑዋቱን ጨምሮ ሦስቱም በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ያሉ ደሴቶች ናቸው። ሁለቱ ሃገራትም ማክሮኔዢያና ፓፑዋ ኒው ጊኒ ናቸው።

"ለሴቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮችና ጉዳዮች በሃገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጪ አካል ውስጥ ውክልና የላቸውም" ስትል ያስሚን ትናገራለች።

Image copyright Chris Morgan/BBC
አጭር የምስል መግለጫ የቀድሞዋ ፓርላማ አባል ሄልዳ ሊኒ

በሃገሪቱ ያሉ ምክር ቤቶች ሁሉም ወንዶች በሆኑ የአካባቢ አለቆች የሚመራ ሲሆን ለፓርላማ አባልነት በእጩነት የሚቀርቡትን የሚጠቁሙትም እነሱው ናቸው።

"በሃገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩት በወንዶች ነው። እጩዎችን እራሳቸው ይጠቁማሉ፤ የሚወዳደሩት እነሱው ስለሆኑ እነሱው ይመረጣሉ። በዚህም ፓርላማው ሙሉ ለሙሉ በወንዶች ይያዛል" ሲሉ የመጀመሪያዋ የቫኑዋቱ ሴት የቀድሞ የፓርላማ ሊኒ አባል ይናገራሉ።

የቀድሞዋ የፓርላማ አባል አክለውም በሕግ አውጪው ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች አለመኖር በሃገሪቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እያስከተለ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህም በቤት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት የሚመለከተውና እስካሁንም በአግባቡ ተግባር ላይ አልዋለም የሚሉትን የቤተሰብ ጥበቃ ሕግ ለማውጣት ዘጠኝ ዓመታትን እንደፈጀ በምሳሌነት ያነሳሉ።

በአሁኑ ጊዜ በቫኑዋቱ የሚገኙ ሴቶች በፆታዎች መካከል ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠን እንዲያበቃ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።

ከሐይማኖታዊ አስተምህሮ አንጻር የወንዶች የበላይነት በስፋት በሚታይባት ቫኑዋቱ፤ ወንዶች ሴቶች ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ የመውሰድና የማስተዳደር ሁኔታ የተለመደና በስፋት የሚታይ ነገር መሆኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ተመልክቷል።

ልጃቸውን ወደ ፓርላማ ይዘው የመጡት አባል ከምክር ቤቱ ተባረሩ

አብዛኛው ሕዝቧ በድህነት ውስጥ የሚኖርባት ይህች ሃገር ዕድገትን ለማምጣት የምትፈልግ ከሆነ በፆታዎች መካከል ያለውን የሰፋ ልዩነት መፍትሄ ልታበጅለት እንደሚገባ የዓለም ባንክ መክረዋል።

275 ሺህ ያህል ብቻ ሕዝብ ባላት ቫኑዋቱ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ወንጀሎች ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። "ከሦስት ሴቶች አንዷ አስራ አምስት ዓመት ከመድረሷ በፊት አንድ አይነት ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባታል" ትላለች ያስሚን።

ያስሚን አክላም በእስር ላይ ከሚገኙ ታራሚዎች 60 በመቶ የሚደርሱት ወሲባዊ ወንጀል የፈጸሙ ሲሆኑ፤ 90 በመቶው በሴቶች ላይ የሚያጋጥሙ ጥቃቶች በሚያውቋቸው ሰዎች አማካይነት እንደሚፈፀሙ ትናገራለች።

Image copyright Chris Morgan/BBC
አጭር የምስል መግለጫ የሴቶች ብቻ ፓርቲ የመሰረቱት ሴት ፖለቲከኞች

በቫኑዋቱ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ተጽዕኖዎችን ለማስቀረት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በፖለቲካው መስክ ያለውን የወንዶች የበላይነት ለመለወጥ በእድሜ ጠና ያሉ ሴቶች ተሰባስበው ሴቶች ብቻ አባል የሆኑበት ፓርቲ መስርተዋል።

በቀድሞዋ የፓርላማ አባል ሄልዳ ሊኒ የሚመራው ይህ ፓርቲ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ሴቶች እንደሚሳተፉ ያሳወቁ ሲሆን ከሃገሪቱ ፓርላማ መቀመጫዎች ግማሹ ለሴቶች ብቻ እንዲደረግ ቅስቀሳ እያደረጉ ናቸው።

በዓለም ላይ በፓርላማቸው ውስጥ ከግማሽ በላይ ሴት እንደራሴዎች ያሏቸው ሃገራት ሦስት ብቻ ናቸው። እነሱም አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ 61 በመቶ ሴት የፓርላማ አባላትን በመያዝ ከዓለም ቀዳሚ ስትሆን፤ ኩባ በ53.2 በመቶ ሁለተኛ ቦሊቪያ በ53.1 በመቶ ሦስተኛ ናቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ