የኬንያ አንድ ግዛት ባለሥልጣናት መቃብር አስቆፍረው የደንብ ልብስ ወሰዱ

ተቆፍሮ የወጣው የደንብ ልብስ Image copyright The Standard
አጭር የምስል መግለጫ ተቆፍሮ የወጣው የደንብ ልብስ

ምዕራብ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ባለሥልጣናት ከመንግሥት የተሰጠውን የደንብ ልብስ እንደለበሰ ከተቀበረ አንድ ግለሰብ አስከሬን ላይ የደንብ ልብሱን ለመውሰድ መቃብሩን ማስቆፈራቸው ተዘገበ።

ማርቲን ሺኩኩ አሉኮዬ የተባለው ግለሰብ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ውሃ ውስጥ ሰምጦ ሲሞት የካካሜጋ ግዛትን የወጣቶች አገልግሎት የደንብ ልብስን እንደለበሰ ነበር።

ኬንያ ውስጥ ታየ የተባለው "ኢየሱስ" ማን ነው?

ምንም እንኳን የሟች ቤተሰቦች ድርጊቱን ቢቃወሙም የአካባቢው ባለሥልጣናት አስከሬኑን ቆፍረው በማውጣት የደንብ ልብሱን ወስደዋል።

የሟቹ አሉኮዬ አጎት እንዳሉት ባለሥልጣናቱ "የሃገሪቱን ሕግና የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ደንብ ጥሰዋል" ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

"የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በምንፈጽምበት ወቅት የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ተሳትፈዋል፤ እነሱም ሟች ከነ ደንብ ልብሱ እንዲቀበር የቀረበው ሃሳብን ፈጽሞ አልተቃወሙትም ነበር" ሲሉ አጎት ፍራንሲስ ሙታምባ ለዴይሊ ኔሽን ተናግረዋል።

ቤተሰቦችም ከ31 ዓመቱ ሟች ልጃቸው ላይ የደንብ ልብሱን ለመውሰድ በባለሥልጣናት የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቃውመውት የነበረ ሲሆን ባለስልጣናቱ ግን የቤተሰቡን ፈቃድም ሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ሳያገኑ ነው መቃብሩን ቆፍረው የወሰዱት።

ለኬንያ ፓርላማ የተላከው ጭነት ባዶውን ተገኘ

አንድ ባለሥልጣን ድርጊቱን አውግዘው መቃብሩን ባስቆፈሩት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"አስከሬን ከተቀበረ በኋላ ቆፍሮ ለማውጣት ማንም ሰው ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊኖረው ይገባል። የግዛቲቱ ባለሥልጣናትም የደንብ ልብሱን ለማስመለስ ሲሉ ከሕግ ውጪ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል" ብለዋል ባለሥልጣኑ።

ሟች አባል የሆነበት ጎሳ ሽማግሌዎችም የአካባቢው ባለሥልጣናትን ድርጊት ያወገዙ ሲሆን ድርጊቱንም "ነውር" ብለውታል።

ልጃቸውን ወደ ፓርላማ ይዘው የመጡት አባል ከምክር ቤቱ ተባረሩ

"በባህላችን መሠረት ውሃ ውስጥ ሰምጦ የሞተ ሰው መቀበር ያለበት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ስለሆነ ደንቡን ተከትለን ነበር የቀበርነው። ባለሥልጣናቱ ግን ለደንብ ልብሱ ሲሉ አስከሬኑን ቆፍረው አውጥተውታል" ብለዋል አንድ የጎሳው ሽማግሌ።

ባለሥልጣናቱ የደንብ ልብሱን ከአስከሬኑ ላይ ገፈው ከወሰዱ በኋላ የአካባቢው ሽማግሌዎች የሟች ቤተሰብን ለማጽናናት አስፈላጊውን ባህላዊ ሥነ ሥርዓት አከናውነው አዲስ ልብስ በማልበስ እንዲቀበር አድርገዋል።

ተያያዥ ርዕሶች