ካስተር ሰሜኒያ፡ «ሴት ስፖርተኞች ደግፈውኝ አያውቁም»

የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪቃዊት ካስተር ሰሜኒያ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪቃዊት ካስተር ሰሜኒያ

የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪቃዊቷ ካስተር ሰሜኒያ 'ሴት ስፖርተኞች ከጎኔ ቆመው አያውቁም' ስትል ቅሬታዋን አሰምታለች።

በ800 ሜትር ለሃገሯ ደቡብ አፍሪቃ ሶስት ጊዜ ወርቅ ያመጣችው ሰሜኒያ ወርሃ መስከረም ዶሃ ላይ በሚካሄደው ውድድር ላይ እንደማትሳተፍ ታውቋል። ምክንያቱ ደግሞ ለሴት አትሌቶች ከሚፈቀደው በላይ የቴስቴስትሮን ሆርሞን ውስጥ አለ በመባሉ ነው።

«ዒለማ የሆንኩት ልሸንፍላቸው ስላልቻልኩ ነው» ስትል የ28 ዓመቷ የ800 ሜትር ሯጭ ሃሳቧን ሰጥታለች።

«የስፖርቱን ዓለም ከተቀላቀልኩ ወዲህ ድጋፍ አግኝቻለሁ ብዬ አላስብም፤ በተለይ ደግሞ በሴት የሙያ አጋሮቼ።»

ጆሃንስበርግ ውስጥ በተካሄደ የሴቶች ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበረችው ሰሜኒያ «በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተቀናቃኞቼ ይህንን ምክንያት ይዘው ሲመጡ ሳይ፤ ምን ብዬ ልጥራው. . .ብቻ አስደሳች ያልሆነ ምክንያት ነው።»

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር [አይኤኤፍ] እርሷንና ሌሎቹ አትሌቶች በውስጣቸው ያለው የቴስቴስትሮን ሆርሞን መጠን በሕክምና እንዲቀነስ ተደርጎ እንዲወዳደሩ ወይም ወደ ሌላ ርቀት እንዲቀይሩ የሚያዘውን ህግ በመቃወም ስትሟገት ቆይታለች።

ሰሜኒያ፤ በቀጣዩ ክረምት ቶክዮ ላይ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር መሳተፍ እና ማሸነፍ ከቻለች በሶስት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ወርቅ በማምጣት ታሪክ ትሠራለች። ነገር ግን ውሳኔው በፍርድ ቤት እጅ ነው የሚገኘው።

አይኤኤፍ ሁለት ጊዜ ሆርሞኗን በመድሃኒት ካልቀነሽ አትወዳደሪም በሚል ከውድድር ውጭ ያረጋት ሲሆን ለዚህም ውሳኔ ይግባኝ ጠይቃለች።

«በመስኩ በጣም ምርጧ ነኝ። የዓለም ምርጥ ሆነሽ ስትገኝ ሰዎች የምታደርጊውን ነገር ሁሉ መከታተል ይጀምራሉ።»

«እኔ ችግር የሆንኩት በጣም ስኬታማ ስለሆንኩ ነው። ሰዎች ደግሞ ሊያስወግዱኝ ይፈልጋሉ።»

«እኔን ማስቆም የሚፈልግ ሰው ከመሮጪያ መስመሩ ላይ ጎትቶ ሊያስወጣኝ ይችላል። ሌላ የምለው ነገር የለኝም። የምነግራችሁ ነገር ቢኖር እኔ የመጨዋቸው ሜዳ ላይ መሆኔን ነው።»

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ