ሂዩማን ራይትስ ዎች፡ ወደ ባሕረ ሰላጤው የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን እንግልት

የአደጋ ጊዜ ጃኬት Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ከሰጠመው ጀልባ የመጣ እንደሆነ የታመነበት የአደጋ ጊዜ ጃኬት በሊቢያ የባህር ዳርቻ ተገኝቷል

ቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ-ሰላጤ መስመርን ተጠቅመው ወደ የመን የሚያቀኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከፍተኛ እንግልትና ብዝበዛ እየገጠማቸው እንደሆነ 'ሂዩማን ራይትስ ዎች' የተሰኘው የመብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።

ሳዑዲ አራቢያ ከደረሱ በኋላም ለከፋ ስቃይ እንደሚዳረጉና በግዴታ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ድርጅት ዕለተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የኢትዮጵያም ሆነ የየመን እና ሳዑዲ አራቢያ ባለሥልጣናት ችግሩን ለመፍታት የወሰዱት እርምጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲልም ድርጅቱ ወቅሷል።

የትኞቹ ሃገራት ከፍተኛ ስደተኛ አላቸው?

ባለፉት አሥር ዓመታት ሥራ አጥነት፣ ድርቅ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሸሽተው ከሃገር የወጡ ኢትዮጵያዊያን እጅግ በርካታ ናቸው ይላል መግለጫው በዘገባው። ስደተኞች ቀይ ባሕርን በጀልባ አቋርጠው በየመን በኩል ሳዑዲ ለመግባት አቅደው እንደሚነሱ ተገልጿል።

ወደ ሳዑዲ ከሚጓዙት የሚልቁቱ ሕጋዊ ወረቀት ሳይዙ ወደ ጅዳ እንደሚዘልቁ ድርጅቱ ያትታል።

«በርካታ ኢትዮጵያዊያን የማይነገሩ እጅግ ሰቅጣጭ ሁኔታዎችን አልፈው ነው ሳዑዲ ለመግባት የሚሞክሩት። ባሕር ውስጥ ከመስጠም ጀምሮ ሊታሰቡ እንኳኝን የማይችሉ ስቃዮችን ያስተናግዳሉ» ይላሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ አጥኚ ፌሊክስ ሆርን።

«ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ሰውነታቸው ላይ ካለው ልብስ በቀር ምንም ሳይዙ ወደ ሃገር ቤት የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያንን ሊደግፍ ይገባል።»

ድርጅቱ 12 ከሳዑዲ የተመለሱ ኢትዮጵያዊያንን አዲስ አበባ ላይ አግኝቶ ስላሳለፉት ሕይወት አናግሯቸዋል። ከስደተኞች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሠሩ ግለሰቦች ዘገባው ውስጥ ተካተዋል።

የዛሬ 2 ዓመት ገደማ የሳዑዲ መንግሥት ሕጋዊ ያልሆኑ ያላቸውን የሌሎች ሃገራት ዜጎች ባስወጣ ጊዜ 500 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሳዑዲ አራቢያ ይኖሩ እንደነበር የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት [አይኦኤም] መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ያሳፈረችው ጀልባ ሰጠመች

ከግንቦት 2009 - መጋቢት 2011 ባለው ጊዜ 260 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ በግዳጅ እንዲወጡ እንደተደረገ ይገመታል። በግዳጅ ማስወጣቱ አሁንም እንደቀጠለ 'ሂዩማን ራይትስ ዎች' ይናገራል።

ኢትዮጵያዊያኑ የሚከተሉት መስመር ጅቡቲ፣ ሶሚሊላንድ፣ ፑንትላንድ፣ የመን እና ሳዑዲ አራቢያን የሚያካልል ሲሆን ሕገ-ወጥ የሰው ደላሎች ስደተኞችን በተለያየ መንገድ በማስፈራራት ገንዘብ እንዲያስልኩ እንደሚያደርጉ ድርጅቱ ያደረገው ጥናት ያሳያል።

«ጅልባዋ ላይ 180 ሰዎች ነበርን፤ 25 መሞታቸውን አስታውሳለሁ» 'ሂዩማን ራይትስ ዎች' ካናገራቸው መካከል አንድ ተመላሽ ይናገራል። «ማዕበሉ እጅግ ሲያንገላታን ነበር። በዚህም ጀልባዋ ልትሰጥም ሲሆን ደላሎቹ ወደ ባሕሩ ይወረውሩን ጀመር። አይናችን እያየም 25 ያህሉን ወደ ባሕሩ ወረወሯቸው።»

ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ከሚያዘዋውሩ ዶላሎች መካከል ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙበት የሚናገሩት ተመላሾቹ የበርካታ ስደተኞች ቤተሰቦች መሬት ወይም ከብት በመሸጥ ገንዘብ ለደላሎች እንደሚልኩ ይናገራሉ።

'ሂዩማን ራይትስ ዎች' ከዚህ በፊት የሳዑዲ ወታደሮች ወደብ ላይ በሕገ ወጥ መንገድ ሊገቡ የሚሞክሩ ሰዎችን እየተኮሱ እንደሚገድሉ ዘግቦ ነበር። ድርጅቱ ያናገረው አንድ ተመላሽም ቦታው በሬሳ የተሞላና የቀብር ሥፍራ እንደሚመስል ይገልፃል።

በሊቢያ የስደተኞች ጀልባ ሰምጦ ተሳፋሪዎቹ የገቡበት ጠፋ

ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ የሚገኙ እሥር ቤቶች እጅግ የላሸቁ፣ ምግብ እና መፀዳጃ የሌላቸው እንደሆኑ ተመላሾቹ ይናገራሉ።

በርካታ ተመላሾች ያለምንም ንብረት ባዶ እጃቸውን የሚመለሱና ለትራንስፖርት እንኳ የሚሆን ገንዘብ የሌላቸው እንደሆኑ ድርጅቱ መታዘቡን ጠቅሷል። የሥነ-ልቦና ቀውስ እና ከበድ ያለ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ፈጣን ሕክምና እንደሚደርግላቸው፤ የመጓጓዣ የሌላቸው ደግሞ ደጋፍ እንደሚደርግላቸው የሚናገረው ድርጅቱ መልሶ ማቋቋም ትኩረት ሊነፈገው የማይገባ ጉዳይ እንደሆነ ያሰምራል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ