የሱዳን የቀድሞ የመረጃና ደህንነት ኃላፊ ሳላህ ጎሽ አሜሪካ እንዳይገቡ ታገዱ

የሱዳን የቀድሞ የደህንነት ኃላፊ ሳላህ ጎሽ Image copyright AFP

የሱዳን የቀድሞ የመረጃና ደህንነት ኃላፊ ሳላህ ጎሽ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መታገዳቸው ተገለፀ። የቀድሞ ኃላፊው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የታገዱት በሰብአዊ መብት ጥሰት እጃቸው አለበት በሚል ነው።

እርሳቸው ብቻም ሳይሆኑ ቤተሰባቸውም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እገዳው ተጥሎባቸዋል።

በሱዳን ወታደራዊ ምክርቤቱና ተቃዋሚዎች ተስማሙ

ሳዑዲ አረቢያ ለሱዳን የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ እንደሚያትተው የቀድሞ ኃላፊው ሳላህ፤ የሱዳን ብሔራዊ የፀጥታና ደህንነት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ሰዎችን በማሰቃየት እጃቸው እንዳለበት ተጨባጭ ማስረጃ አለኝ ብሏል።

የቀድሞ የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን እስከተወገዱበት ሚያዚያ ወር ድረስ ከመረጃና ደህንነት ኃላፊው ሳላህ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበራቸው ተገልጿል።

እርሳቸው ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በተቃዋሚዎች ግፊት ምክንያት ኃላፊነታቸውን ለቀዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማይክ ፖምፔዌ፤ ሱዳን በሲቪል የሚመራ መንግሥት እንዲኖራት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ በትዊተር ገፃቸው ላይ መልእክታቸውን አስፍረዋል።

አሁን ሃገሪቷን እያስተዳደረ ያለው ምክርቤት እና የተቃዋሚዎች ጥምረት በሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ ስለሚኖራቸው ኃላፊነት ከአስር ቀናት በፊት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

በሚኖራቸው የሥልጣን ክፍፍል ላይም ለመጨረሻ ጊዜ በመጭው ቅዳሜ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ