አሜሪካ ውስጥ አንድ ታጣቂ ስድስት ፖሊሶችን አቆሰለ

ፖሊሶች ከታጣቂው ቤት አቅራቢያ Image copyright Reuters

አንድ ታጣቂ በአሜሪካዋ ፊላደልፊያ ከተማ ውስጥ ከፖሊሶች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጎ ስድስቱን ካቆሰለ በኋላ መያዙ ተዘገበ።

የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው ፖሊሶች ፊላዴልፊያ ከተማ ውስጥ ኒስታውን ቲያጎ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ከዕፅ ጋር የተያያዘ የመጥሪያ ወረቀት ለመስጠት በመጡበት ጊዜ ነው ተብሏል።

ታጣቂው በፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍቶ የተኩስ ልውውጡ ለሰባት ሰዓታት ያህል ከተካሄደ በኋላ ግለሰቡ እጅ በመስጠቱ ፍጥጫው አብቅቷል።

በቴክሳሱ ጅምላ ጥቃት 20 ሰዎች ሞተዋል

የኦሃዮው ታጣቂ እህቱንና ስምንት ሰዎችን ገደለ

ሞውሪስ ሂል የተባለው የ36 ዓመቱ ጎልማሳ እጁን ወደላይ አንስቶ ከቤቱ ሲወጣ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የታዩ ሲሆን የተጠርጣሪው ጠበቃም ግለሰቡ እጁን እንዲሰጥ እንዳግባቡት ተናግረዋል።

በአካባቢው የደረሱት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት ከግለሰቡ ቤት መውጫ አጥተው የነበሩ ሁለት የፖሊስ ኣባላትንና ሦስት ሌሎች ሰዎችን ነጻ ማውጣታቸው ተገልጿል።

ተጠርጣሪው በርካታ ሽጉጦችና ከፊል አውቶማቲክ ጠመንጃ ታጥቆ እንደነበር ፖሊስ ገልጾ፤ ታጣቂው በአካባቢው በነበሩ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት ላይ ከቤት ውስጥ ሆኖ ሲተኩስ እንደነበረ ተብሏል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ግለሰቡ ከፖሊሶች ጋር ያደርግ የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ክስተት በፌስቡክ ላይ በቀጥታ ያስተላልፈው ነበር።

በተኩስ ልውውጡ ለህይወት አስጊ ያልሆነ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት የፖሊስ መኮንኖች ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውም ታውቋል።

የአካባቢው የፖሊስ ባለስልጣን እንደተናገት "በዚህ የተኩስ ልውውጥ በርካታ የፖሊስ መኮንኖች አለመገደላቸው እንደተአምር የሚቆጠር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከክራይስትቸርች የመስጊድ ጥቃት በተአምር የተረፈው ኢትዮጵያዊ

በፍጥጫው ወቅት በመኪና የተገጨ አንድ ሌላ ፖሊስ ግን ህክምና እየተከታተለ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የዋይት ሃውስ ፕሬስ ክፍል ኃላፊ ሆጋን ጊድሊ እንደገለጹት ፖሊሶች ስለቆሰሉበት ስለዚህ ክስተት ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

ይህ የተኩስ ልውውጥ ያጋጠመው በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎችን ከገደሉና ካቆሰሉ ከጥቂት ሳምንት በኋላ በጦር መሳሪያ ላይ የሚደረግ ቁጥጥርን በተመለከተ የሚደረገው ክርክር እየጠነከረ በመጣበት ጊዜ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች