ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር እንደማትደራደር አሳወቀች

ኪም ጆንግ ኡን Image copyright Reuters

ሰሜን ኮሪያ "በደቡብ ኮሪያ ያልተገባ ድርጊት ምክንያት" በሚል ሰበብ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልታደርግ የነበረውን ቀጣይ ድርድር እንደማታካሂድ አሳወቀች።

ሰሜን ኮሪያ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷን ያሳወቀችው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢን ትናንት ሐሙስ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ አርብ ሰሜን ኮሪያ ሁለት ሚሳኤሎችን ወደ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻዋ በመተኮስ ሙከራ ማድረጓን የደቡብ ኮሪያ ሠራዊት አሳውቋል። ይህም ሙከራ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

ሰሜን ኮሪያ ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች

ይህ ተከታታይ የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ የተደረገው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ባደረጉት ውይይት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማስወገድ ውይይት ለመጀመር ከተስማሙ በኋላ ነው።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሃገራቸው ከጃፓን ነጻነቷን ያገኘችበትን ቀን በተከበረበት ወቅት ሁለቱ ኮሪያዎች በአውሮፓዊያኑ 2045 እንደሚዋሃዱ በመናገራቸው ነው ሰሜን ኮሪያ ቁጣዋ የተቀሰቀሰው።

በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግር "ለራሱና ለምሥራቅ እስያ ብሎም ለዓለም ሰላምና ብልጽግናን የሚያመጣው አዲሱ የኮሪያ ልሳነ ምድር ከፊታችን እየጠበቀን ነው" ሲሉም ተናግረዋል- ፕሬዝዳንቱ።

ኪም ጆንግ ኡን የደቡብ ኮሪያን መሬት በመርገጥ የመጀመሪያ ሆኑ

ሰሜን ኮሪያ፣ ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ እያካሄዱት ባለው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን ይህም ከፕሬዝዳንት ትራምፕና ከሙን ጃኢን ጋር ቀደም ሲል ያደረጉትን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን በመግለጫዋ ላይ ጨምራ ገልጻለች።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ከፍተኛ ወጪ ስለሚወጣበት የደቡብ ኮሪያና የአሜሪካ የጦር ልምምድ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር።

የሰሜን ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት አካባቢውን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነጻ ለማድረግ የተጀመረው ንግግር መቋጫ እንዳያገኝ ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምዱን ማድረጓ ዋኛው ምክንያት ነው ሲሉ ተናግረዋል።