የቴክሳስ ፖሊስ ልማደኛዋን ድንኳን ሰባሪ እየፈለገ ነው

ጥንዶች የጋብቻ ቀለበት ሲያጠልቁ Image copyright NADTOCHIY

የአሜሪካ ፖሊስ በደቡብ ቴክሳስ ውስጥ በየሠርግ ቤቱ እየተዘዋወረች በርካታ ስጦታዎችን ሰርቃለች የተባለችን 'ድንኳን ሰባሪ' ሴት እያፈላለኩ ነው አለ።

ማንነቷ ያልታወቀውና እየተፈለገች ያለችው ሴት ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ ቢያንስ አራት የሰርግ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሳትጋበዝ በመገኘት ለሙሽሮች የተበረከቱ ስጦታዎችን ዘርፋለች።

ፖሊስ ግለሰቧን ለመያዝ እንዲረዳው ለአዲስ ተጋቢዎች የተሰጠን የስጦታ መግዣ ኩፖንን በአንድ መደብር ውስጥ ልትጠቀምበት ስትል የተነሳ የተጠርጣሪዋን ፎቶግራፍ አሰራጭቷል።

በደቡብ ወሎ ሙሽራና ሚዜውን የገደለው ቦምብ

በተጨማሪም ፖሊስ ሴትዮዋ ያለችበትን ለሚጠቁመው ሰው የ4 ሺህ ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ብሏል።

የኮማል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባወጣው መግለጫ "ይህችን ልማደኛ ድንኳን ሰባሪ ለሕግ በማቅረብ የሌሎችን ሰዎች የደስታ ቀን እንዳታበላሽ እናድርግ" ሲል ጥሪ አቀርቧል።

በአካባቢው ያለ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን የሚያዘጋጅ አንድ ድርጅት ኃላፊ እንደተናገረው የግለሰቧን ፎቶ ከተመለከተ በኋላ እንደሚያውቃት ተናግሯል።

በግለሰቧ ተዘርፈናል ከሚሉት አዲስ ተጋቢ ጥንዶች መካከል የሆኑ ባልና ሚስት እንደተናገሩት ንብረት እንደተወሰደባቸው ያወቁት በጫጉላ ሽርሽር ላይ ሳሉ እንደነበርና ስሜታቸው እንደተጎዳና የደስታ ጊዜያቸው እንደተበላሸም ገልጸዋል።

ሙሽሪት እጮኛዋ መቃብር ላይ ድል ባለ ሠርግ ተሞሸረች

ጥንዶቹ ድንኳን ሰባሪዋን ሴት ለይተው ያወቋት ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች በጥሬ ገንዘብና በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠር ዶላር የሚመነዘሩ ቼኮችና የስጦታ ኩፖኖችን እንደሰረቀቻቸው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ባጋጠማቸው ነገር የተበሳጨችው ሚስት ፍሎሪስ ግለሰቧ "ፍቅራችንን ግን ልትሰርቅ አትችልም" በማለት ፖሊስ ድንኳን ሰባሪዋን አግኝቶ ሕግ ፊት እንደሚያቀርባት ያላትን ተስፋ ገልጻለች።