ሶልቭ አይቲ ኢኖቬሽን : የዘንድሮው የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ዛሬ ይታወቃሉ

ወጣቶች በፈጠራ ሥራ ላይ Image copyright iCog Labs FB

በሶልቭ አይቲ ኢኖቬሽን (Solve IT Inovation) ሲካሄድ የነበረው የዘንድሮው ሃገር አቀፍ የወጣቶች የፈጠራ ሥራ ውድድር አሸናፊዎች ዛሬ ይፋ እንደሚደረጉ የአይኮግ ላብስ (iCog Labs) መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ ለቢቢሲ ገለፁ።

ሶፊያ ከዐብይ አሕመድ ጋር የራት ቀጠሮ ይዛለች

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሶልቭ አይቲ ኢኖቬሽን በተባለ ፋውንዴሽን [አይኮግ ላብስና ሌሎች ተባባሪ ድርጅቶች ተካተው የሚያዋቅሩት] በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ18-28 በሚደርሱ ወጣቶች መካከል የፈጠራ ውድድር ያካሂዳል።

ዋነኛ ዓላማውም በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ትኩረት ያላደረገና በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ማውጣትና ሥራዎቻቸው ተግባር ላይ እንዲውሉ ማሰልጠን፣ መደገፍና ለውጤት ማብቃት ነው።

ውድድሩ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የመጡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶችን፤ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ከሚገኙ እና በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰር አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ሥራ አስኪያጁ ገልፀውልናል።

በባለፈው ዓመት የተካሄደውን ውድድር የአሜሪካ ኤምባሲና አይኮግ ላብስ በጋራ በመሆን ሲያዘጋጁት የዘንድሮውን ዓመት ውድድር ደግሞ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ጃይካና አይኮግ ላብስ በጋራ በመሆን አዘጋጅተውታል።

ዘንድሮም ከመላው ሃገሪቱ የተመዘገቡ ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው ለውድድር ቀርበዋል።

የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ላይ ወደ 1500 የሆኑ ተመዝጋቢዎች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ውድድር ላይ ግን ቁጥሩ ጨምሮ ወደ 2800 የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው ለመጨረሻው ዙር ውድድር የደረሱት 160 ወጣቶች መሆናቸውን ከአቶ ጌትነት ሰምተናል።

63 የፈጠራ ሥራዎችም ለውድድሩ እንደቀረቡ ገልፀውልናል።

ከየክልሉ አዲስ አበባ የመጡ ተወዳዳሪዎች የካምፕ ቆይታ፣ ሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ ተቋማትን የመጎብኘት አጋጣሚው ነበራቸው።

ከሁሉም ክልሎች የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ከአዲስ አበባ የመጡት ግን ቁጥራቸው ከፍተኛ ነበር ብለዋል።

የውድድር ማስታወቂያውን ያወጡትም በዲጂታል ቴክኖሎጂ [ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራምና የመሳሰሉት] ሲሆን በአይኮግ ላብስ ድረ-ገፅ ላይ ገብተው እንዲሞሉ ይደረጋል ፤ ይህም ወጣቶቹ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እንዲሞሉ ለማስቻል ሲሆን በዚህ ዘዴ የተጠቀሙም አንድ ነጥብ ያገኛሉ።

አዲስ አበባ፡ የፈጠራ ማዕከል ለመሆን እየጣረች ያለች ከተማ

አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች በትምህርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም በጤና እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን እንዳቀረቡ የሚናገሩት አቶ ጌትነት "በዚህ ዘመን እርሻ መታረስ የነበረበት በቴክኖሎጂ ነበር" ይላሉ።

በተለይ በጤናው ዘርፍ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ሥራዎች እንደሚበራከቱ ይናገራሉ። ከጋምቤላም እንዲሁ ያላቸውን ባህላዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓት በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የሠሩ ወጣቶች እንደቀረቡም ነግረውናል።

ባለፈው ዓመት አንድ ኦክስጅን የሚያስፈልገው ታማሚ የሚወስደውን የኦክስጅን መጠን የሚቆጣጠር የፈጠራ ሥራ ያቀረበው ወጣት ያሸነፈ ሲሆን [ከጅማ] የ75 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኖ ነበር።

በዚያው ውድድርም ሁለተኛ ደረጃን የያዘው [ከመቀሌ] የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ሥራን ያቀረበ ሲሆን በሦስተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ [ከባህር ዳር] 'Hello Reminder' የተባለ ዕቃና ህፃናት ቢጠፉ በሞባይል አማካኝነት ያሉበትን የሚያሳውቅ የፈጠራ ሥራ ቀርቦ ነበር።

ለእነርሱም የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸው አቶ ጌትነት አስታውሰዋል።

ውድድሮቹ በገለልተኛና ከድርጅቱ ውጭ ባሉ ባለሙያዎች እንደሚዳኝም አክለዋል።

በዘንድሮው ውድድርም ለተሳተፉት በሙሉ የምስክር ወረቀትና ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለሚወጡት ፕሮጀክቶች የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ የአሜሪካና የጃፓን ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና እንግዶች በተገኙበት በቃና አዳራሽ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ አቶ ጌትነት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ