ሦስት ሰዎች የሞቱበት የውጫሌው ግጭት መነሻ ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ካርታ

በደቡብ ወሎ ዞን፤ አምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ በአካባቢው ወጣቶችና በፀጥታ ኃይል መካከል በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ ለቢቢሲ ገለጸ።

የወረዳው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መኮንን ሹሙ እንደተናገሩት ሐሙስ ዕለት ባጋጠመው በዚህ ክስተት ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በግጭቱ ከሞቱት ሌላ አምስቱ ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በደሴ ሆስፒታልና በሌሎች የጤና ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑም ተገልጿል።

ሁሉን 'አርሂቡ' የምትለው ደሴ

ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ግጭት የተፈጠረው ለአርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሎ ለመንግሥት ሠራተኞች የተሰጠ መሬት እንደሆነ ዋና ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ደግሞ ይህ ግጭት ከመፈጠሩ አንድ ቀን ቀድሞ ማለትም ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ቦታውን ለመለካት የሄዱ ባለሙያዎች በአካባቢው ወጣቶች ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ይህንን የፈፀሙ ወጣቶች በፖሊስ መታሰራቸውን ይናገራሉ።

ይህ ለቤት መስሪያነት የተሰጠው ቦታ የሚገኘው ከውጫሌ ከተማ ሦስት ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን ልዩ ስሙም አበጋር ሜዳ ተብሎ የሚታወቅ ነው።

ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ከአካባቢው ለተነሱ አርሶ አደሮች የመሬት ካሳ መከፈሉን የሚያስታውሱት ዋና ኢንፔክተር መኮንን፤ ግጭቱ የተከሰተው የከተማው ማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ቦታውን በመለካት ላይ ሳሉ ወጣቶች ተሰባስበው በመምጣታቸው ነበር ብለዋል።

• ሁለት እምነቶችን በአንድ ጣራ ለአስርታት ያሳደሩ ጥንዶች

በወቅቱ የወረዳው የፀጥታ አካላት በቦታው ተገኝቶ ለማረጋጋት ሞክርው የነበረ ቢሆንም "ወጣቱ ሆ! ብሎ በመውጣት የፀጥታ ኃይሉ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ" ይላሉ።

ፖሊስ ሁኔታውን ለማረጋጋት የተኩስ ድምፅ ቢያሰማም "የወጣቶቹ ጥያቄ ቦታውን ልቀቁልን የሚል ስለነበር፤ ሰላም ከተፈጠረ ብለን ቦታውን ለቀን ወጥተናል" ሲሉ ጉዳዩን በትዕግስት ለማለፍ መሞከራቸውን ያስረዳሉ።

በዚህም ጸጥታ አስከባሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቦታውን ሲለኩ የነበሩ ባለሙያዎችን ጭምር ይዘው አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ያስረዳሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉትም የመጀመሪያውን ክስተት ተከትሎ በማግስቱ 'መሬቱ ለእኛ ነው የሚገባን' የሚሉ ወጣቶች ተሰባስበው ሰልፍ እንዳካሄዱና የታሰሩ ወጣቶችንም ለማስፈታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራታቸውን ይናገራሉ።

ቴክቫህ ኢትዮጵያ፡ የፀረ ጥላቻ ንግግር የወጣቶች እንቅስቃሴ

የወረዳው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊም እንደሚሉት የፀጥታ ኃይሎቹ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ ግን ወጣቶቹ ቁጥራቸውን ጨምረው [እርሳቸው እንዳሉት በግምት 300 የሚሆኑ] በመምጣት "በአምባሰል ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ እስረኞችን ለማስፈታት ሙከራ ማድረጋቸውን" ገልፀውልናል።

ጥይት መተኮሱንና ፖሊስ ጣቢያውም በድንጋይ መደብደቡን ጠቅሰው፤ ፖሊስም ይህንን ለመከላከል ጥረት ማድረጉን ይናገራሉ። በክስተቱ ሕይወታቸው ያለፈና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ከማን በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ እንደማያውቁ ነግረውናል።

በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ወጣቶቹ ከፀጥታ ኃይሎቹ ጋር መጋጨታቸውን እንደተመለከቱና "አካባቢው በተኩስ ተናወጠ፤ ሁሉም እግሬ አውጭኝ ሆነ" በማለት ክስተቱን ገልጸውታል።

ነዋሪዎቹ በግጭቱ የሦስት ሰዎች ሕይወት ያለፈ መሆኑን ገልጸው በርካቶች እንደቆሰሉ "የወደቁትን ያነሳነውም ተኩሱ ከበረደ በኋላ ነው" ብለዋል።

በተኩሱ ሕይወታቸውን ያጡትም ሆነ ጉዳት ያጋጠማቸው የግጭቱ አካል ያልነበሩና በነዋሪዎቹ አጠራር 'ተባራሪዎች' ያሏቸው ንፁሃን ሰዎች መሆናቸውን ነግረውናል።

የቤተሰቦቹን መሬት ለማስመለስ ሕግ ያጠናው ወጣት

በተከሰተው ግጭት ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው ተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ዋና ኢንስፔክተር መኮንን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ውጫሌ ከተማ ዛሬ የገበያ ቀን መሆኑን በመጥቀስ በአንፃራዊ ሁኔታ አካባቢው መረጋጋቱንና ችግሩን ለመፍታት የዞን የፀጥታ ኃይሎች ከነዋሪዎችጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ መኮንን ሹሙ አክለዋል።

ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ከግጭቱ በኋላ በአካባቢው የፌደራል ፖሊስና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የተሰማራ መሆኑን ገልፀው ዛሬ ከተማዋ መረጋጋቷን ገልጸዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ