አሜሪካ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ መያዣ አወጣች

መያዣ የወጣባት ግሬስ 1 ነዳጅ ጫኝ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ መያዣ የወጣባት ግሬስ 1 ነዳጅ ጫኝ

ጅብራልተር ውስጥ ተይዞ የነበረው የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብ እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ የአሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት መርከቡ ተይዞ እንዲቆይ የመያዣ ትዕዛዝ አወጣ።

ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንደምትጭን የተነገረላት ግሬስ 1 የተባለችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሶሪያ ነዳጅ እያመላለሰች ነው በሚል ጥርጣሬ ነበር ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የተያዘችው።

መርከቧ ተይዛ እንድትቆይ አሜሪካ ሙከራ ብታደርግም ጥያቄው በጅብራልታር ተቀባይነት ሳያገኝ ሐሙስ ዕለት ውድቅ ተደርጎ ነበር።

መርከቧ በተያዘችበት ጊዜ ኢራን ድርጊቱ "ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት ነው" በማለት ተቃውማው ነበር።

እንግሊዝ የነዳጅ መርከቧ በኢራን በመታገቱ ስጋት ገብቷታል

ኢራን የአሜሪካ የቅኝት ድሮንን መትታ ጣለች

ትራምፕ ጦርነት ከተጀመረ ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች ሲሉ አስጠነቀቁ

ኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከቧ መያዟን ተከትሎ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የነበረችውን የእንግሊዝ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ሥር አውላ ነበር።

ኢራን መርከቧ የዓለም አቀፉን የባሕር ደንብ በመተላለፏ ነው የያዝኳት ብትልም በርካቶች ግን የአጸፋ ምላሽ እንደሆነ በስፋት ሲናገሩ ቆይተዋል።

አሜሪካ የኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከብ ከጫነችው ነዳጅ ዘይት ጋር ተይዛ እንድትቆይ የጠየቀችው ኢራን ዓለም አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ የኢኮኖሚ ድንጋጌን፣ የባንክ ማጭበርበርን፣ ሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠርና የሽብርተኝነት ሕጎችን በመጥቀስ ነው።

በተጨማሪም ፓራዳይዝ ፍሎባል ትሬዲንግ የተባለው ድርጅት አሜሪካ የውጪ ሃገር የሽብር ድርጅት ነው ብሎ ከሰየመው ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ስሙ ባልተጠቀሰ የአሜሪካ ባንክ ውስጥ ያለው 995 ሺህ ዶላር እንዳይንቀሳቀስም የአሜሪካ መንግሥት አዟል።

የጅብራልተር አስተዳዳሪዎች እንደተናገሩት የኢራን ባለስልጣናት መርከቧ የአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ወደ ጣለባቸው ሃገራት እንደማትጓዝ ማረጋገጫ ሰጥተውናል ብለዋል።

አሜሪካ እንዳትለቀቅ ብትጠይቅም በዳኛው ውሳኔ መሰረት አስፈላጊውን ዝግጅቷን መርከቧ ካጠናቀቀች ዛሬ ወይንም ነገ ጉዞዋን እንደምትጀምር ተገልጿል።

እንግሊዝም ሆነች ጅብራልተር አሜሪካ ስላወጣችው የመያዣ ትዕዛዝ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።