የቻይና ዜጎች የኬንያዊያንን ባህላዊ መጠጥ ሲያመርቱ ተያዙ

ሁለቱ ቻይናዊያን Image copyright DCI Twitter

የኬንያ ፖሊስ ቻንጋ የተባለውን የኬንያዊያን ባህላዊ የአልኮል መጠጥን በከፍተኛ መጠን በድብቅ ሲያመርቱ ነበር ያላቸውን ቻይናዊያን መያዙን አስታወቀ።

ቻይናዊያኑ ማቻኮስ በተባለው አካባቢ በሚገኝ ቤት ውስጥ ባህላዊውን የአልኮል መጠጥ እንደሚያጣሩ ፖሊስ ከነዋሪዎች ባገኘው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ፍተሻ ከፍተኛ መጠን ያለው መጠጥና ለመጠጡ መስሪያ የሚውሉ ግብዓቶችን መያዙን ታውቋል።

የኬንያ ማዕከላዊ የምርመራ አገልግሎት እንዳስታወቀው ተጠርጣሪዎቹ ዋንግ ያላን እና ዋንግ ሃይጂያን የተባሉ ቻይናዊያን እንደሆኑ አስታውቋል።

ቻይናዊው በዘረኛ ንግግሩ ምክንያት ከሃገር ሊባረር ነው

ለኬንያ ፓርላማ የተላከው ጭነት ባዶውን ተገኘ

በእነዚህ ቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ውስጥም 800 ሊትር ሜታኖል፣ 3ሺህ ሊትር ያለቀለት የአልኮል መጠጥ፣ የአልኮል ድፍድፍ የያዙ በርካታ በርሜሎች፣ ትላልቅ የውሃ ማጠራቀሚያዎችና ለአልኮሉ መስሪያ የሚውሉ የእህል አይነቶች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ፖሊስ እንዳለው ባህላዊውን መጠጥ በከፍተኛ መጠን እንደ ፋብሪካ ለማምረት የሚያስችል መሳሪያዎችንም በተጠርጣሪዎቹ ቤት ውስጥ አግኝቷል።

Image copyright DCI Twitter

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ያሉት ሁለቱ ቻይናዊያን ቤት ውስጥ ከተገኙት ነገሮች መካከል ሜታኖል የተባለው ለመጠጡ ማምረቻነት የሚውለው ኬሚካል አደገኛ ሲሆን ሰዎች በቀላሉ እንዲሰክሩ ያደርጋል።

ከዚህ ቀደም በቤት ውስጥ በሚዘጋጁ ባህላዊ መጠጦች ሰበብ ሕይወታቸው ላለፈና የዓይን መታወር ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እንደ ዋነኛ ምክንያት ሜታኖል በመጠጡ ዝግጅት ወቅት ጥቅም ላይ በመዋሉ እንደሆነ ይታመናል።

ልጃቸውን ወደ ፓርላማ ይዘው የመጡት አባል ከምክር ቤቱ ተባረሩ

ቻይናዊያኑ በድብቅ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማያውቀውን የኬንያዊያንን ባህላዊ መጠጥ ቻንጋን በፋብሪካ ደረጃ አምርተው በማሸግ ለገበያ እያቀረቡ እንደነበር ይጠረጠራል።

ለዚህም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምንጩ ከየት እንደሆነ የማይታወቅ በጠርሙስ የታሸገ የቻንጋ ፎቶ በስፋት ሲዘዋወር መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በሕገወጥ መንገድ ቤታቸው ውስጥ የአልኮል መጠጥ በማምረትና በማከማቸት ተጠርጥረው የተያዙት ሁለቱ ቻይናዊያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ኬንያ መግባታቸው ባለመታወቁ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን ሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ተገልጿል።

ተያያዥ ርዕሶች