አፍሪቃውያን፤ አሜሪካ እና አውሮጳ ዚምባብዌ ላይ የጣሉትን ዕገዳ እንዲያነሱ እየወተወቱ ነው

ዚምባብዌ ውስጥ አንድ አነስተኛ ዳቦ 2 ዶላር [58 ብር ገደማ] ያወጣል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ዚምባብዌ ውስጥ አንድ አነስተኛ ዳቦ 2 ዶላር [58 ብር ገደማ] ያወጣል

16 የአፍሪቃ ሃገራት ዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮጳ ሕብረት ዚምባብዌ ላይ የጣሉትን ዕግድ 'በአስቸኳይ' እንዲያነሱ በመወትወት ላይ ናቸው።

የሳድቅ [የደቡባዊ አፍሪቃ ዕድገት ማሕረበሰብ] የወቅቱ ሊቀ-መንበር የሆኑት የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ዕገዳው ከዚምባብዌ አልፎ ቀጣናውን እየጎዳው ነው ብለዋል።

ዕገዳው የተጣለው በጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር 2002 ላይ ሲሆን የወቅቱ የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ነበሩ።

የሙጋቤ ምትክ የሆኑት ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናጋግዋ የሃገሪቱን ዕድገት ያደቀቁ ፖሊሲዎች ሲሉ ዕገዳዎቹን ተችተዋል።

በዕገዳው ምክንያት የውጭ ሃገራት ድርጅቶች ወደ ዚምባብዌ ገብተው መሥራት አይችሉም። ዚምባብዌ በተቃራኒው በከፋ የኑሮ ወድነት እና በመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት በመዳከር ላይ ትገኛለች።

የአንድ ዳቦ ዋጋ ባለፈው ሚያዚያ ከነበረው በአምስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት 5 ሚሊዮን ገደማ ዚምባብዌያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚሹ ይናገራል።

መጋቢት ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 'በሃገሪቱ ተጨባጭ የፖለቲካ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ዕገዳውን አናነሳም' በማለት ዕገዳውን በአንድ ዓመት ማራዘማቸው አይዘነጋም።

141 ገደማ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና እና ድርጅቶች ወደ አሜሪካ መግባትም ሆነ መገበያያት እንደማይችሉ ሮይተርስ የተሰኘው የዜና ወኪል አሳውቋል።

የገዢው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሮበርት ሙጋቤ እና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ወደ አውሮጳም ሆነ አሜሪካ መጓዝ አይችሉም። አልፎም በመንግሥት እጅ ያሉ ድርጅቶች ምጣኔ ሃብታዊ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።

በሙጋቤ እግር የተተኩት ምናንጋግዋ ሃገር ቤት ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው ይገኛል። ባለፈው ሳምንት አገዛዙን ተቃውመው የወጡ ሰልፈኞችን ፖሊስ በኃይል በትኗል። የምናንጋግዋ ተቃዋሚዎች 'ኑሮ ከሙጋቤ ዘመን በላይ ከፍቷል' ሲሉ ይተቿቸዋል።

ሳድቅን እየመሩ የሚገኙት ማጉፉሊ መዲናቸው ዳሬሳላም ላይ በተሰናዳ ስብሰባ ላይ ነው ዚምባብዌ አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ ስላለች ዕገዳው ሊነሳ ይገባል የሚል ሃሳብ የሰነዘሩት።

ፀረ-መውለድ ፍልስፍናን ያውቁታል?

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ