በሠርጉ ላይ ቦንብ ፈንድቶ ወንድሙና 62 የሞቱበት አፍጋናዊ ተስፋ ቆርጧል..

ሚራዋይስ ኤልሚ Image copyright Reuters

በአፍጋኒስታኗ መዲና ካቡል የአጥፍቶ ጠፊ ኢላማ የነበረው ሠርግ ለብዙዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሲሆን ሙሽራው ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ገልጿል።

ሙሽራው ሚርዋይስ ኤልሚ ለሃገሪቱ ቴሌቪዥን እንደተናገረው ምንም እንኳን በዚህ የቦንብ ጥቃት ሙሽራዋ ብትተርፍም ወንድሙና ሌሎች ዘመዶቹ ከተገደሉት 63 ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

በካቡል ሠርግ ላይ በተወረወረ ቦንብ የ63 ሰዎች ህይወት አለፈ

ከ125 በላይ የተጠፋፉ ኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦችን ያገናኘችው አሜሪካዊት

ሚርዋይስ ለቶሎ ኒውስ እንደተናገረው ለሠርጉ የመጡ ሰዎችን በፈገግታ ሲቀበሉ ቆይተው ከሰዓታት በኋላ አስከሬናቸው ከአዳራሹ ሲወጣ ማየት እንዳቆሰለው ተናግሯል።

"ቤተሰቤም ሆነ ሙሽራዬ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ናቸው፤ መናገር እንኳን አይችሉም። ሙሽራዬ በተደጋጋሚ ራሷን እየሳተች ነው" በማለት ተናግሯል።

"ተስፋ ነው የቆረጥኩት፤ ወንድሜን፣ ጓደኞቼንና ዘመዶቼንም አጥቻለሁ። በህይወቴ ዘመን ደስታን በጭራሽ እንደማላገኝ አውቃለሁ" ብሏል።

"ለቀብራቸው መሄድ አልችልም፤ በጣም ዝያለሁ። ለአፍጋናዊያን ይህ የመጨረሻው ሰቆቃ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ሥቃያችን ይቀጥላል" በማለት በመሪር የሃዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ተናግሯል።

የሙሽራዋ አባትም አስራ አራት የቤተሰብ አባሎቻቸውን እንዳጡ ለአፍጋን ሚዲያ ተናግረዋል።

“ከተማ አስተዳደሩ የወሲብ ንግድን በህግ ወንጀል የማድረግ ስልጣን የለውም” የህግ ባለሙያ

አይ ኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ሲሆን፤ ከሞቱት በተጨማሪ 180 ሰዎች ቆስለዋል።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ ጥቃቱን "አረመኔያዊ" ተግባር ሲሉ አውግዘውታል።

ከዚህም በተጨማሪ ለአሸባሪዎች በር ከፍተዋል በማለት ታሊባንንም ወንጅለዋል።

ከአሜሪካ ጋር በሰላም ውይይቶች ላይ እየተደራደረ ያለው ታሊባንም ጥቃቱን አውግዞታል።

Image copyright Reuters

ምን ተከሰተ?

ቦንቡ የፈነዳው ቅዳሜ ምሽት 4፡40 ገደማ ሲሆን ሥፍራው ደግሞ የሺአ ሙስሊሞች የሚያዘውትሩት የካቡል ምዕራባዊ ክፍል ነው ተብሏል።

ታሊባንና አይኤስን ጨምሮ የሱኒ ሙስሊም ፅንፈኞች በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን የሚገኙትን የሺአ ሙስሊሞችን በተደጋጋሚ ለጥቃቶቻቸው ኢላማ አድርገዋቸዋል።

በጥቃቱ ቆስሎ ከሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የ23 ዓመቱ ሙኒር አህመድ የአጎቱ ልጅ ከሟቾቹ ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግሯል።

ፀረ-መውለድ ፍልስፍናን ያውቁታል?

"ፍንዳታው ሲከሰት ታዳሚዎች እየጨፈሩና በደስታ ላይ ነበሩ" በማለት ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግሯል።

"ፍንዳታውንም ተከትሎ ከፍተኛ ግርግር የተፈጠረ ሲሆን፤ ብዙዎች እየጮሁና እያለቀሱ ነበር" ብሏል።

ወንዶች እና ሴቶች ለየብቻ ሆነው የሚስተናገዱበት የአፍጋኒስታን የሠርግ ሥነ-ሥርዓት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደሙበታል።

ተያያዥ ርዕሶች