አማራ ክልል፡ መተማ ዮሐንስ በተያዙት ተሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው

ከተሽከርካሪዎቹ አንዱ Image copyright Social Media

የመከላከያ ሠራዊት ንብረት ናቸው የተባሉና በመተማ ዮሐንስ በኩል ጭነት ይዘው ወደ ሱዳን ሊሻገሩ ሲሉ እንዲቆሙ በተደረጉ አምስት ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ ገለጸ።

ትናንት ከሰዓት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ አምስት የመከላከያ ሠራዊት ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ሱዳን ለመሻገር ሲሞክሩ መተማ ዮሐንስ ላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ ታግደው እንዳያልፉ መደረጋቸውን በስፋት እያነጋገረ ይገኛል።

ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎችና ፎቶግራፎች እንደሚጠቁሙት ጭነት የያዙት ከባድ ተሽከርካሪዎች ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ተከበው መንገድ ዳር እንደቆሙና የአካባቢው ባለስልጣናትም ስለጭነቱ ህጋዊነት ለማወቅ የማጣራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ያመለክታሉ።

ባሕር ላይ ያለምግብና መጠጥ 11 ቀናት ያሳለፈው ኢትዮጵያዊ

ቢቢሲ ስለክስተቱ ለማወቅ ባደረገው ጥረት የመተማ ዮሃንስ ሁሉን አቀፍ የወንጀል ምርመራ ኦፊሰር የሆኑትን ሳጅን እንዳልካቸው ተሰማን በማናገር እንደተረዳው አምስቱ ከባድ ተሽከርካሪዎች እሁድ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወደ ሱዳን ለመሻገር ሲሞክሩ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች አሽከርካሪዎቹን ፓስፖርት እንዲያሳዩ መጠየቃቸውንና ማሳየት እንዳልቻሉ ተገልጿል።

ሳጅን እንዳልካቸው አክለውም "ይህንን ተከትሎ አለመግባባት መፈጠሩንና በዙሪያው የነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የተሽከርካሪዎቹ ጭነት በሕገ ወጥ መልኩ ሊሻገር ነው በሚል ጥርጣሬ እንዳይንቀሳቀሱ አድርገው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገዋቸዋል" ብለዋል።

ምንም እንኳ ፖሊስ ተሽከርካሪዎቹን ባገኘበት ጊዜ እንደተባለው ሆኖ ባያገኘውም "ሌላኛው የጥርጣሬ መነሻ ደግሞ የተሽከርካሪዎቹ የሰሌዳ ቁጥር በግሪስ ተቀብቶ እንዳይታይ ተደርጓል" የሚል እንደነበርም ሳጅን እንዳልካቸው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አምስቱም ተሽከርካሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው የአካባቢው የመስተዳድር አካላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ማጣራት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የወንጀል ምርመራ ኦፊሰሩ ተሽከርካሪዎቹ የጦር መሳሪያ የጫኑ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናገረዋል።

''ውጤቱ ለእኔ ደመወዜ ነው" ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ብሩክ እናት

ከባድ ተሽከርካሪዎቹ የተወሰነ ቁጥር ባላቸውና የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስና መለዮን የለበሱ ጠባቂዎች አጅበዋቸው እንደነበር ቢነገርም እስካሁን ግን ሙሉ መረጃ የሌላቸው መሆኑን ሳጅን እንዳልካቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክስተቱን ተከትሎ መተማ ላይ ተይዘው እንዳያልፉ የተደረጉት ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ዘረፋ እንደተፈጸመ እየተነገረ መሆኑን ጠቅሰን የጠየቅናቸው የፖሊስ ኃላፊው በሰጡን ምላሽ "በተፈጠረው ግርግር የጸጥታ ችግርም ሆነ ዘረፋ አላጋጠመም" ሲሉ አረጋግጠዋል።

ፖሊስ ስለተያዙት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ምንነትና ወደየት እያመሩ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ሳጅን እንዳልካቸው እስካሁን ከከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት ባለስልጣናት የተባሉት ነገር እንደሌለ ጠቅሰው "በዚሁ አካባቢ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትም ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለው ነግሮናል" ብለዋል።

ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የመተማ ዮሐንስ ከተማ የአስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ ኢንስፔክተር ይናገርን ብንደውልላቸውም ለጊዜው ያላቸው መረጃ ከዚህ የተለየ አለመሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ሁሉም ተሽከርካሪዎች በአንድ ቦታ ሆነው ጥበቃ እየተደረገላቸው ሲሆን ጉዳዩን ለማጣራት የዞንና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ወደ ስፍራው መጓዛቸውን ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ለበቀል የተነሳች ሴት በአንድ ኃላፊ ላይ የአሲድ ጥቃት ፈጸመች

አክለውም የተያዙት ከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች ሕጋዊ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥ ደብዳቤ እንዳላቸው መናገራቸውንና እስካሁን ግን የደብዳቤውን ሕጋዊነት ማረጋገጥ አለመቻሉን የአስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የአካባቢው የፀጥታ ኃላፊዎች እንዳሉት ክስተቱን ተከትሎ በአካባቢው ምንም አይነት የፀጥታም ሆነ የትራንስፖርት መስተጓጎል እንደሌለና ከሱዳን ወደ መተማ ዮሐንስና ከመተማ ዮሐንስ ወደ ሱዳን ገላባት የሚደረገው እንቅስቀሴም እንደቀጠለ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።

ስለተሽከርካሪዎቹ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመከላከያ ሠራዊት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ለጊዜው አልተሳካልንም።

ተያያዥ ርዕሶች