አሜሪካ፡ 'እርጉዝ እንደነበርኩ አላወቅኩም' ያለችው እናት ነፃ ወጣች

የ21 ዓመቷ አል ሳልቫዶራዊት ኸርናንዴዝ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ኸርናንዴዝ ወንጀሉን ፈፅማለች ተብላ ከተያዘች ጀምሮ እሥር ቤት ለ33 ወራት ከርማለች

የገዛ ልጅሽን መፀዳጃ ቤት ወስጥ ገድለሽ ጥለሻል ተብላ ተከሳ የነበረችው የ21 ዓመቷ ኤል ሳልቫዶራዊት ነፃ ወጣች።

ኸርናንዴዝ ሆዷን ከፉኛ ሲቆርጣት ወደ ሽንት ቤት ታመራለች። እዚያም እያለች ራሷን ትስታለች። ወደ ሆስፒታል ስትወሰድ ዶክተሮች 'ልጅ ወልደሻል ነገር ግን በሕይወት የለም' ይሏታል። ኸርናንዴዝ 'ወንዶች በቡድን ሆነው ደፍረውኛል፤ እኔ እርጉዝ መሆኔን አላወቅኩም ነበር' ስትል ላለፉት 33 ወራት ብትከራከርም ሰሚ አላገኘችም ነበር።

አቃቤ ሕግ የሴቲቱ ጥፋት 40 ዓመት ያስቀጣል ሲል ቢሞግትም አልተሳካለትም።

የኸርናንዴዝ ጉዳይ ዓለምን በአግራሞት ሰቅዞ የያዘ ጉዳይ ነበር። በተለይ የሴት መብት ተሟጋቾች ለ21 ዓመቷ ወጣት እናት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ከርመዋል።

ላቲን አሜሪካዊቷ ኤል ሳልቫዶር ውርጃን በተለመከተ ጥብቅ ሕግ ካላቸው የዓለም ሃገራት አንዷ ነች። በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውርጃ ማካሄድ አይፈቀድም። ይህን ፈፅመው የተገኙ ከ2-8 ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል።

የኸርናንዴዝ ክስ እንዲህ ሊከር የቻለው ውርጃ ብቻ ሳይሆን የነብስ ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች ተብላ በመከሰሷ ነው። ጥፈተኛ ሆና ብትገኝ በትንሹ የ30 ዓመት የከርቸሌ ኑሮ ይጠብቃት ነበር ተብሏል።

«ክብሩ ይስፋ፤ ፍትህ አግኝቻለሁ» ስትል ነበር ከውሳኔው በኋላ መፈናፈኛ ላሳጧት የሚድያ ሰዎች ስሜቷን የገለፀችው።

ኸርናንዴዝ ወንጀሉን ፈፅማለች ተብላ ከተያዘች ጀምሮ እሥር ቤት ለ33 ወራት ከርማለች። «ሕልሜ ትምህርቴን መቀጠል ነው። ደስተኛ ነኝ» ብላለች ሲል ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል ፅፏል።

ኤል ሳልቫዶር ውስጥ ነፃ ከወጣችው ሴት በፊት ተመሳሳይ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ሕይወታቸውን ከፍርግርጉ ጀርባ እየመሩ የሚገኙ በርካታ ሴቶች እንዳሉ ይነገራል። የኸርናንዴዝ ነፃ መውጣት ለእነዚህ ሴቶች ትልቅ ተስፋ እንደሆነ የሕግ ሰዎች የመብት ተሟጋቾች ያትታሉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት 'ለኤል ሳልቫዶር ሴቶች ትልቅ ድልን ያጎናፀፈ ፍርድ' ሲል ብይኑን ገልፆታል።