መርማሪዎች፡ 'ኦማር አል-ባሽር ከሳዑዲው ንጉስ ሚሊዮን ረብጣዎች ተቀብለዋል'

ኦማር አል-ባሽር Image copyright AFP

የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር ሐሰን አል-በሽር ከሳዑዲ አረቢያ ሚሊዮን ዶላሮች ተቀብዋል ሲሉ መርማሪዎች የአል በሽርን ጉዳይ ለያዘው ፍርድ ቤት አሳውቀዋል።

አል በሽር ዕለተ ሰኞ የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል ሂደት ለመከታተል ፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር። ጠበቃዎቻቸው ግን 'መሬት ያልረገጠ ውንጀላ' ሲሉ ተቃውመውታል።

ለ30 ዓመታት ሃገራቸው ሱዳንን የመሩት አል በሽር በርካታ ወራት ከፈጀ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ከሥልጣን እንዲወርዱ ተደርገዋል።

ኦማር አል-በሽር: ከየት ወደየት?

ባለፈው ሰኔ አቃቤ ሕግ የአል በሽር ቤት ውስጥ የታጨቁ የውጭ ሃገር ጥሬ ገንዘቦች አግኝቻለሁ ሲል ማሳወቁ አይዘነጋም።

ነጭ ሽርጣቸውን ለብሰው፤ ራሳቸው ላይ የተለመደች ፎጣቸውን ጠምጥመው ፍርድ ቤት የተገኙት አል በሽር በፍርድ ሂደቱ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

ፍርድ ቤቱ ስምዎትን ያረጋግጡልኝ ሲል በጎ ምላሽ የሰጡት አል በሽር የት ነው የሚኖሩት ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሳቅ የታጀብ ምላሽ ሰጥተዋል፤ «ቀድሞ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት፤ አሁን ደግሞ ኮባር እስረ ቤት» የሚል።

መርማሪ አሕመድ አሊ ሞሐመድ፤ ኦማር አል-ባሽር ከሳዑዲው አልጋ ወራሽ 25 ሚሊዮን ዶላር መቀበላቸውን አምነዋል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። አልፎም መጠናቸው ያልታወቀ ገንዘቦች ከሌሎች የሳዑዲ ቱጃሮች ተቀብለዋል ሲሉ የምርመራቸውን ውጤት ይፋ አድርገዋል።

የአል በሽር ጠበቆች 'ደንበኛችን ገንዘቡን መቀባላቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም' ሲሉ ተከራክረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች