ባለማዕረግ ተመራቂው እና በ3ዲ ፕሪንተሩ የፈጠራ ሥራ ያሸነፈው መልካሙ

መልካሙ ታደሰ የፈጠራ ሥራውን ሲያሳይ Image copyright Melkamu Tadesse

"በእውነቱ የተወለድኩበት ቦታ የመኪና ድምፅ ብቻ ነበር የሚሰማው፤ ያውም ትላልቅ መኪና ሲያልፍ" ይላል። የተወለደው በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ልዩ ቦታው ከላቻ የተባለ ሥፍራ ነው- የማዕረግ ተመራቂውና የዘንድሮው ሶልቭ አይቲ የፈጠራ ሥራ ውድድር አሸናፊ መልካሙ ታደሰ።

የመልካሙ ቤተሰቦች አርሶ አደሮች ናቸው።

ያሉበት ነባራዊ ሕይወት ሳይበግራቸው እርሱም ሆነ ወንድሞቹ ማንኛውም የገጠር ተማሪ በሚያሳልፈው የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

እርሱ እንደሚለው የሚማሩበት ትምህርት ቤት የ40 ወይም 50 ደቂቃ መንገድ በእግር ያስጉዛል። ተራራና ሸለቆውን አቆራርጠው ነበር ትምህርት ቤት የሚደርሱት።

የመንገዱ ርቀት ብቻ ሳይሆን በጠዋት ተነስቶ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎችን (ላም ማለብ፣ ከብቶችን ማሰማራት) ማከናወንም ይጠበቅበታል። ይህን ማድረጉ ግን መልካሙን ከዓላማው አልገታውም።

የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ

በዚህ ሁኔታ እየተማረ ከክፍል ክፍል ሲዘዋወር የአንደኝነትን ደረጃ የሚወስድበት አልነበረም።

ከዚያም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መካኒካል ምህንድስና አጠና። በዚህ ዓመት በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብም በማዕረግ ተመርቋል።

እውቀቱንና ችሎታውን ለማሳደግ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል ሌሎችን ማስጠናት፣ ማስተማርና ማለማመድ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ። ያወቀውን ለሌሎች ለማካፈል በሚያደርገው ጥረት ውስጥ እርሱ እንደሚማር ይገልፃል።

"አባቴ በኢኮኖሚ አቅም ማጣት ምክንያት ነው ያልተማረው" የሚለው መልካሙ ቁጭታቸውን እርሱ እንዲወጣላቸው ግን አደራ ይሉት እንደነበር ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ወንድሞቹም ሆኑ አባቱ ባላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ ያደርጉለት ነበር። "አባቴ ውጤታማ ሆኜ በማየቱ እጅግ ደስተኛ ነው፤ ደስታውን ከወዳጆቹ ጋር ለመጋራት ድግስ ለመደገስ እየተዘጋጀ ነው" ይላል።

አሁን ደግሞ ሶልቭ አይቲ ባዘጋጀው የፈጠራ ሥራ ውድድር አሸናፊ በመሆን ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። የፈጠራ ሥራው ባለ ሦስት አውታር ማተሚያ (3ዲ ፕሪንተር) ነው።

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

ይህ ለዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ፅሁፉ የወጠነው የፕሮጀክት ሃሳብ ነው።

የሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት አለባቸው ብሎ የሚያምነው መልካሙ በተማረበት ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ባለ ሦስት አውታር ፕሪንተር ባለመኖሩ ተማሪዎች ፕሮጀክቶቻቸውን ለመሥራት ሲቸገሩ ያስተውላል።

በእርግጥ ይህ የማተሚያ ማሽን ገበያ ላይ አለ። መልካሙ እንደሚለው ግን ዋጋው ውድ በመሆኑ በቀላሉና እንደልብ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት አይገኝም። ይህንን ችግር ለመፍታት የእርሱ የፕሮጀክት ሃሳብ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳል።

በተለይ የህንፃ ዲዛይነሮች እንዲሁም ሌሎችም ንድፋቸውን በእርሳስ ከመሳል ባሻገር የህንፃውን ምስል በሦስቱም ማዕዘን ቁልጭ ብሎ እንዲወጣ የሚያትሙበት ማሽን ነው። ሃሳቡ የመጣለትም ከዚሁ ችግር በመነሳት ነው።

ከዚያም ከሁለት የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቹ መንበሩ ዘለቀ እና መልካሙ ፈቃዱ ጋር በጋራ በመሆን የፈጠራ ሥራውን ማጎልበት ጀመሩ። በውድድሩ ለመጨረሻው ዙር ከቀረቡት 63 ሥራዎች መካከልም አንዱ ለመሆን በቃ።

Image copyright Melkamu Tadesse

በሶልቭ አይቲ ፋውንዴሽን ሥልጠናዎችንና ልምዶችን ለመቅሰም እድል አገኙ። ይህም የፈጠራ ሥራቸውን በድል ለማጠናቀቅ መንገድ ከፈተላቸው።

በመሆኑም የመልካሙና ጓደኞቹ የ3ዲ ፕሪንተር ፕሮጀክት በአንደኝነትን ደረጃ አጠናቋል።

ፕሪንተሩ የተሰራው በአካባቢያቸው በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች ሲሆን ቤተሰቦቹና ዩኒቨርሲቲ በሚማርበት ጊዜ አማካሪው የነበሩት አቶ ሔኖክ እገዛ እንዳደረጉላቸው ሳይጠቅስ ግን አላለፈም።

3ዲ ፕሪንተር

የዚህ ፕሮጀክት የቡድን መሪ የሆነው መልካሙ እንደሚለው ፕሪንተሩ አዲስ ግኝት አይደለም። ከውጭ አገር በአርባ ሺህ ብር መግዛት እንደሚቻል መረጃው ያለው ይሁን እንጂ የእነርሱ የፈጠራ ሥራ ጠቅላላ ወጪ በጥሬ ገንዘብ ሲገመት 6 ሺህ አምስት መቶ ብር ብቻ ነው የወሰደው።

ማተሚያ ማሽኑ ባለሦስት አውታር ማተሚያው [3ዲ ፕሪንቲንግ]፤ የታዘዘውን ምስል በብዕር መሳይ ነገር የሚስል [CNC Plotting]፣ ሌዘሪንግ (በጨረር መሳይ ዘዴ) በአንድ ጊዜ ማከናወን የሚችል ነው።

ከዚህም ባሻገር ማሽኑ ሦስት የኮምፒዩተር ቋንቋዎችን [C++C፣ Language and Machine language] በአንድ ጊዜ ማንበብ የሚችል ነው።

"ፕሮጀክቱ ከባድ ነው፤ የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን እውቀት የሚጠይቅ ነው" የሚለው መልካሙ የመካኒካል ምህንድስና፣ የኤሌክትሪካል ምህንድስና፣ የኤሌክትሮኒክ እውቀት፣ የሶፍትዌር፣ የኮምፒዩተር ኮዲንግ እውቀት ይጠይቅ እንደነበር ያስረዳል።

ሀና እና ጓደኞቿ የሠሩት የእናቶች ምጥ መቆጣጠሪያ

ይህንን ጥምረት በእነዚህ ዘርፎች ላይ ከተሰማሩ ጓደኞቹ ጋር በመተባበር በመፍጠርና በኢንተርኔት ላይ ያሉ ሥልጠናዎችን በመከታተል ከግባቸው መድረስ እንዲችሉ አስተዋፅኦ አድርጎላቸዋል።

"የአሜሪካ እና የጃፓን ኤምባሲ አምባሳደሮችም ይህንን በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተሰራውን ፕሪንተር ጎብኝተው መሥራቱን አረጋግጠዋል" ይላል መልካሙ።

በዘንድሮው ውድድር ወደ 2800 የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው 160 ወጣቶች ለመጨረሻው ዙር ውድድር የደረሱ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ በቡድንም በግልም እየሆኑ በአጠቃላይ 63 የፈጠራ ሥራዎችን አቅርበዋል።

3ዲ ፕሪንተር የፈጠራ ሥራም በአንደኝነት ደረጃ ተሸላሚ ሆኗል።

በአይኮግ ላብ ድርጅት የ100 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ወደፊት ከሃገር ውስጥና ከውጭ አገር ያሉ ባለሃብቶች ጋር በመገናኘት የፈጠራ ሥራቸውን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰሩ መልካሙ ታደሰ ገልፆልናል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ የአሜሪካና የጃፓን ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና እንግዶች በተገኙበት በቃና አዳራሽ መካሄዱ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ