በአንድ ስም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገብ እንደማይችሉ ምርጫ ቦርድ ገለፀ

ነጋ ጃራና ዳውድ ኢብሳ

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግና በአባ ነጋ ጃራ የሚመራው ኦነግ ቀደም ሲል ተዋህደው አንድ እንደሚሆኑ አስታውቀው ነበር።

በቅርቡ ግን ሁለቱም በኦነግ ስም ከምርጫ ቦርድ እውቅና ለማግኘት የምዝገባ ሂደት መጀመራቸው ተሰምቷል። ጉዳዩን በማስመልከት ቢቢሲ ያናገራቸው የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ "እኛ የምናውቀው የምርጫ ቦርድ የሚጠይቀውን ሁሉ ህግ አሟልተን መግባታችንን ነው። እንደሕጉ ከሆነ ከመመዝገብ የሚከለክለን ነገር የለም። ውሳኔው የምርጫ ቦርድ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አንድ ለመሆንና ለመዋሃድም እየሰራን ነው። ኦነግን በተመለከተ ግን እኛም የኦሮሞ ሕዝብም የሚያውቀው አንድ ኦነግ ነው ያለው" ብለዋል።

ኦነግ ከመንግሥት ጋር ያደረኩት ስምምነት አልተከበረም አለ

''ኦነግ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ አገር ቤት ይገባል''

የሌላኛው ኦነግ መሪ አባነጋ ጃራ ደግሞ "ምርጫ ቦርድ መመዝገብ ሕጋዊ ግዴታችን ነው። መመዝገብ ስላለብንም ነው ሂደቱን የጀመርነው። ኦነግን አንድ ድርጅት የማድረግ ሥራ ግን የፖለቲካ ሥራ ነው። እየተነጋገርንበት ነው። በቅርቡ ጨርሰን አንድ ንግግር እናደርገዋለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"አንድ ድርጅት መዝግቡኝ ስላለ የሚመዘገብ አይደለም፤ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። የፓርቲ ፕሮግራምን ማስኬድ፣ ቃለ ጉባኤ ማየትና የጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ የሚባሉት ነገሮች ማለቅ አለባቸው። እነሱ ካለቁ በኋላ ነው ለቦርዱ ለውሳኔ የሚቀርበው" በማለት ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ስም እንመዝገብ ማለታቸው ውሳኔ የሚያገኝበትን መንገድ የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ አብራርተዋል።

ኦነግ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ማወጁን ገለፀ

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሁለቱም እዚህ ደረጃ ላይ አልደረሱም የሚሉት ወ/ሮ ሶሊያና በዚህ ውዝግብ ለማንም የተሰጠ የስም እውቅና አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ሁለቱም ግን 'ኦነግ' ነው ስማችን ብለው የምዝገባ ሂደት እንደጀመሩ እናውቃለን የሚሉት አማካሪዋ በአንድ ስም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገብ እንደማይችሉም ተናግረዋል።

በስም ይገባኛል ሂደቱም አንደኛው ቀድሞ ሂደቱን ስለጀመረ ሁለተኛውን አንተ አይመለከትህም ማለት እንደማይቻልም አማካሪዋ አረጋግጠዋል። ውሳኔ የሚሰጠውም የሁለቱም አመልካቾች ዝርዝር መስፈርት ከታየ በኋላ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል።

ተያያዥ ርዕሶች