ሱዳን የሽግግር መንግሥት፡ አብዳላ ሃምዶክ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ

አብደላ ሃምዶክ በካርቱም የፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት ቃላ መሃላ ሲፈፅሙ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግሥታት ይሰሩ ነበር

ሱዳን ለሦስት ዓመታት ለሚቆየው የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ሾመች።

አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ የሽግግር መንግሥቱ መሪ በመሆን ቃለ መሃላ የፈፀሙ ሲሆን በቃለ መሃላቸው በአገሪቱ ያለውን ሰላም ማረጋገጥ እና ለምጣኔ ሐብታዊ ቀውሶች እልባት መስጠት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን አደራዳሪነት የሱዳን ህዝብ እንዴት ይመለከተዋል?

ኦማር አል-በሽር: ከየት ወደየት?

ሌተናነት ጄነራል አብደል ፈታህ አብደልራህማብ ቡርሃን ለሉዓላዊ ምክርቤቱ መሪ ሆነው መምራት ከጀመሩ በኋላ የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ እስከ ቀጣዩ የአገሪቷ ምርጫ ድረስ እንደሚያስተዳድሩ ተገልጿል።

የሉዓላዊ ምክር ቤቱና ሃምዶክ በቃለ መሃላ ሥነስርዓቱ ላይ ሱዳን ኦማር አል በሽር ሥልጣን በኋላ ከወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት የተላቀቀችበት የመጀመሪያው ጊዜ ብለውታል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በበኩላቸው አሁን የተመሰረተው መንግሥት በአገሪቷ የነበረውን የወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት እንዲያከትም ያደርገዋል በማለት ተስፋ ሰንቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሃምዶክ ከአውሮፓዊያኑ 2011 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል።

'አል-ባሽር ከሳዑዲው አልጋ ወራሽ ገንዘብ ተቀብለዋል'

መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው ተግባራት መካከል፤ ጦርነትን ማስቆም፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም መገንባት፣ የምጣኔ ሐብት ቀውስን መፍታት እና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ የውጭ ፖሊሲ መገንባት እንደሆኑ ሃምዶክ ለሮይተርስ ዜና ወኪል አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ሃምዶክ የአገሪቷ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሆኑ ከሥልጣን በተወገዱት ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር የታጩ ሲሆን ጥያቄው ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አብደላ ሃምዶክ ማን ናቸው?

• የተወለዱት በሱዳን ኮርዶፋን ግዛት በአውሮፓዊያኑ 1956 ነው።

• ከማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ሦስተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።

• በአውሮፓዊያኑ 1990 በዚምባብዌ የዓለም አቀፉ ስደተኞች መርጃ ድርጅት ( አይ ኦ ኤም) አማካሪ በመሆን ሰርተዋል። ከዚያም በኋላ በአይቮሪ ኮስት በአፍሪካ ልማት ባንክ የፖሊሲ ኢኮኖሚስት በመሆን አገልግለዋል።

የሱዳን ሠራዊትና ተቃዋሚዎች ሥልጣን ለመጋራት ተስማሙ

• በተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ በመሆንም ከአውሮፓዊያኑ 2011 ጀምሮ ሲያገለግሉ ነበር።

ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱና ተቃዋሚዎች የተስማሙት በምን ነበር?

  • የሥልጣን ክፍፍሉ ለ39 ወራት እንዲቆይ
  • የሽግግር መንግሥቱ ስልጣን ሲያበቃ ምርጫ እንዲካሄድ
  • ሉዓላዊ መንግሥት፣ ምክር ቤትና ሕግ አውጭ አካል እንዲመሠረት
  • ጄነራሉ ለ21 ሳምንታት ምክር ቤቱን እንዲመሩ፤ ቀሪዎቹን ጊዜያት ደግሞ የሲቪል መንግሥቱ እንዲያስተዳድር ተስማምተዋል።
  • ሉዓላዊ ምክር ቤቱ 11 አባላት [5 ሲቪል እና 5 ወታደራዊ እና አንድ በጋራ ስምምነት የተካተተ] ያቀፈ እንዲሆን
  • ጠቅላይ ሚንስትሩ በዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች የሚመረጡ ሲሆን ምክር ቤቱን ይመራሉ።
  • የመከላከያ ሚንስትሮች የውስጥ ጉዳይ ኃላፊዎች በወታደራዊ መንግስቱ ይመረጣሉ
  • ሌሎቹ የኃላፊነት ቦታዎች በዲሞክራሲ ደጋፊዎች በተመረጡ እጩዎች ይያዛሉ።
  • የሉዓላዊ ምክርቤቱና የምክርቤቱ አባላት ለምርጫ አይወዳደሩም።

በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ የጀመረው ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ሲሆን አገሪቷን ለ30 ዓመታት ያስተዳደሩት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ ነበር።

የሲቪል መንግሥት እንሻለን የሚሉ የአገሪቷ ዜጎች ለወራት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን በእንዚህ ጊዜያትም የበርካቶች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ